ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስተላለፈው አዲስ ውሳኔ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ምን ያህል ያሰጋል?
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ለሄይቲ እና ለሶሪያ ስደተኞች ተሰጥቶ የነበረውን ጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ (TPS) ያቋረጠበትን እርምጃ የሚደግፍ ውሳኔ አስተላልፏል።
ይህ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በአሜሪካ የመቆየት መብታቸውን ለማስጠበቅ አቤቱታ አቅርበው የመንግሥትን ውሳኔ በጊዜያዊነት ባሳገዱት ኢትዮጵያውያን የፍርድ ሂደት ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው የስደተኞች ሕግ ባለሙያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"Temporary Protected Status" የተባለው ይህ አሠራር ግጭት፣ የተፈጥሮ አደጋ ወይም ሌላ ለደኅንነት አስጊ የሆነ ክስተት ካለባቸው አገራት የሚመጡ ስደተኞች አሜሪካ ውስጥ እንዲቆዩ የሚሰጥ ጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ መብት ነው።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለኢትዮጵያውያን ይህንን ከለላ የሰጡት የትግራይ ጦርነትን ተከትሎ ነበር። ለሦስት ዓመት በቆየው በዚህ ከለላ አምስት ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ እንደሆኑ ተገልጿል።
በስደተኞች ላይ ጠንካራ እርምጃዎችን እየወሰደ ያለው የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ግን ኢትዮጵያ፣ ሄይቲ እና ሶሪያን ጨምሮ ከበርካታ አገራት ለመጡ ስደተኞች የተሰጠውን የዚህን መብት ተፈጻሚነት አቋርጧል።
ታኅሣሥ ላይ ለኢትዮጵያውያን የተሰጠው ከለላ እንዲቋረጥ የወሰነው የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት፤ ስደተኞቹ እስከ የካቲት ድረስ ባለው የ60 ቀናት ገደብ ውስጥ ከአሜሪካ እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥቶም ነበር።
ይሁን እንጂ ሦስት ኢትዮጵያውያን 'አፍሪካ ኮሚዩኒቲስ ቱጌዘር' ከተባለ የአፍሪካውያን ስደተኞች መብት ተሟጋች ቡድን ጋር በመሆን በቦስተን ከተማ ለሚገኝ የፌደራል ፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበዋል። ጉዳዩን የተመለከቱት የፌደራል ዳኛም አቤቱታውን በዝርዝር ለመመልከት ሲሉ እርምጃውን በማገድ የኢትዮጵያውያኑ ቆይታ እንዲራዘም የሚያደርግ ውሳኔ ሰጥተዋል።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትናንት ሐሙስ 18/2018 ዓ.ም. ውሳኔ ያስተላለፈው በተመሳሳይ መልኩ ጊዜያዊ ዕገዳ ተሰጥቷቸው በነበሩት የሄይቲ እና የሶሪያ ስደተኞች ላይ ነው።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች ስድስት ለሦስት በሆነ የድምፅ ብልጫ የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ውሳኔን በመደገፍ ከዚህ ቀደም ከሁለቱ አገራት የመጡት ዜጎች እንዳይባረሩ የተሰጠውን ዕገዳ ቀልብሰዋል።
በዚህም ምክንያት ጊዜያዊ የሕግ ከለላ አግኝተው የነበሩ 350 ሺህ የሄይቲ እና 6,100 የሶሪያ ዜጎችን መብት ለማቋረጥ የተላለፈው የአገሪቱ መንግሥት ውሳኔ ጸንቷል።
የውሳኔው በጽሑፍ ያሰፈሩት ዳኛ ሳሙኤል አሊቶ ጊዜያዊ ከለላው የሚሰጥበት ሕግ፤ አገሪቱ መንግሥት ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚያስተላልፈው ውሳኔ በፍርድ ቤት እንዳይታይ እንደሚከለክል ገልጸዋል።
አቤቱታውን ያቀረቡት የሄይቲ ስደተኞች የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔውያን ያስተላለፈው በዘር መድልኦ እንደሆነ እና እርምጃው ሕገ መንግሥቱን እንደሚጥስ በመግለጽ ያቀረቡት ክስ አሳማኝ እንዳልሆነ ዳኛው ተናግረዋል።
በአሜሪካ ሜኒሶታ ግዛት የስደተኞች ጠበቃ የሆኑት ሙሉዓለም ጌታቸው ይህ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በሂደት ላይ ባለው የኢትዮጵያውያን አቤቱታ ላይም ሊተገበር እንደሚችል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔዎች ውጤት ክሱ በቀረበበት "በአንድ መዝገብ ላይ ብቻ" እንደማያበቃ የሚያስረዱት ጠበቃ ሙሉዓለም፤ "ከዚህ በኋላ የታች ፍርድ ቤቶች ተመሳሳይ ኬዞችን እንደዚህ ነው መመልከት ያለባቸው የሚል መመሪያ ጭምር ነው" ሲሉ የሚኖረውን ተጽዕኖ አብራርተዋል።
የሄይቲ እና ሶሪያን ጉዳይ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወሰደው ውሳኔው ታች እርከን ላይ ባሉ ፍርድ ቤቶች የታገደበት የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ነው።
ሙሉዓለም "የፍትሕ መሥሪያ ቤት [ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት] የወሰደው የሄይቲ እና የሶሪያን ጉዳይ ብቻ ቢሆንም [ውሳኔው] በኋላ ላይ ተግባር ላይ የሚውለው ለሁሉም ነው" ብለዋል።
እንደ ጠበቃው ገለጻ፤ ከዚህ በኋላ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ይህንን ዓይነቱን የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ የማገድ "መብት እንደሌላቸው" ገልጸዋል። ይህንን ውሳኔ ተከትሎም የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤቱ በቀደመው ውሳኔው መሠረት በጊዜያዊነት የቀጠሉትን ሕጋዊ ከለላዎች እንደሚያቋርጥ አክለዋል።
ይሁን እንጂ በዚህ አሠራር ያገኙት ከለላ የተቋረጠቸባው ኢትዮጵያውያን የስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄ በማቅረብ፣ በጋብቻ በሚገኝ የመኖሪያ ፈቃድ፣ 'ስፖንሰር' በሚያደርጓቸው ሰዎች አማካኝነት ወይም በሠራተኝነት ቅጠር በአሜሪካ ሊቆዩ የሚችሉበት 'ጠባብ ዕድል' እንዳለ ጠበቃው አስረድተዋል።
በአንድ መንገድ የተገኘ ከለላ ሲቋረጥ ወደ ሌላ አማራጭ የሚቀየርበት አሠራር ግን "እጅግ ከባድ" መሆኑን አክለዋል።