ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ በትግራይ የሰላም ሂደትን "የሚያደናቅፉ አካላትን" አሳሰበች
በትግራይ የሰላም ሂደትን "እያደናቀፉ ያሉ አካላት" ለውይይት ጥረቶች ትብብር እንዲያደርጉ በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ ማሳሰቢያ ሰጠ።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ የፖለቲካ እና የሲቪል ማኅበረሰብ መሪዎች በፖለቲካ ውይይት ውስጥ መሳተፍ እና የፕሪቶሪያውን ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ሙሉ በሙሉ መተግበር እንዳለባቸው አሳስቧል።
ኤምባሲው ዛሬ ዓርብ ሰኔ 19/2018 ዓ.ም ባወጣው አጭር መግለጫ፣ የሰላም ሂደቱን "በንቃት እያደናቀፉ ያሉ አካላት" ፣ በአፍሪካ ኅብረት ለሚመራ ውይይትን የማበረታታት ጥረቶች "በአስቸኳይ መተባበር አለባቸው" ብሏል።
የአሜሪካ ኤምባሲ ይህን መግለጫ ያወጣው፣ አገሪቱ በኢትዮጵያ ያለውን ሰላም በማናጋት ውስጥ ተሳታፊ ናቸው ባለቻቸው አክራሪ የህወሓት አባላት እና የቅርብ የቤተሰቦቻቸው ላይ የቪዛ ክልከላ መጣሏን ካስታወቀች ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በአክራሪ የህወሓት አባላት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት እንዲያገረሽ የሚያደርግ ውጥረት እየተባባሰ መምጣቱን በመግለጽ ነበር ለዚህ ተጠያቂ ባደረጋቸው አካላት ላይ የቪዛ ክልከላውን የጣለው።
ህወሓት የአሜሪካን የቪዛ ክልከላ "ሚዛናዊ ያልሆነ" ሲል አውግዟል። የአሜሪካ እርምጃ የትግራይን እውነታ እንደማያንጸባርቅ እና የፌደራል መንግሥቱን "ተጠያቂ ያላደረገ" መሆኑን በመጥቀስም ኮንኗል።
የዛሬው አሜሪካ ኤምባሲ መግለጫ፣ የሰላም ሂደቱን "በንቃት እያደናቀፉ ያሉ" ያላቸውን አካላት በስም አልጠቀሰም።
በተለይ ህወሓት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የተቋቋመውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አፍርሶ ከጦርነቱ በፊት በተመረጠው ምክር ቤት ከተካ በኋላ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለው ውጥረት እየተባባሰ ቀጥሏል።
የክልሉ ምክር ቤት በቅርቡ ያወጣው አስገዳጅ ወታደራዊ አገልግሎትን የያዘው አወዛጋቢ አዋጅ ተግባራዊ እንዲሆንም አዟል። አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላዎችም በሰፊው እየተካሔዱ መሆናቸውን ቢቢሲ ከምንጮቹ አረጋግጧል።
ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አቶ ጌታቸው ረዳ እና አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ ህወሓት "በጥቂት ቀናት ውስጥ" ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጀ ነው ሲሉ በቅርቡ ከስሰው ነበር።
ክሱን ውድቅ ያደረገ ህወሓት በበኩሉ፤ በትግራይ ክልል አዲስ ግጭት ለመቀስቀስ እየተዘጋጀ ያለው የፌደራል መንግሥቱ ነው ሲል በተቃራኒው ይከሳል።
በምሥራቅ አፍሪካ የሚደረጉ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ጥረቶችን እንዲያግዙ በኅብረቱ የተሾሙት እና የፕሪቶሪያውን ስምምነት በዋና አደራዳሪነት የመሩት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ሰኔ 4 ወደ መቀሌ አቅንተው ከህወሓት መሪዎች ጋር ተወያይተው ነበር።
ኦባሳንጆ ውይይቱን "ውጤታማ" ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ የህወሓት መሪዎች በበኩላቸው ውይይቱን ከአዲስ አበባ ጋር ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት እንደገና ለመጀመር የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተናግረዋል።
የአሜሪካ ኤምባሲ በዛሬው መግለጫው፣ አሜሪካ በትግራይ ክልል ያለውን የፖለቲካ እና የሰብአዊ ሁኔታ እየተከታተለች እንደምትገኝ ጠቅሷል።
አሜሪካ ለትግራይ ክልል የሚደረገውን ወሳኝ እና የህይወት አድን ሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን መደገፏን እንደምትቀጥል የገለጸው ኤምባሲው፣ በክልሉ ውስጥ ዘላቂ መረጋጋት መኖሩ ደግሞ ለሂደቱ ቀጣይነት ወሳኝነት እንዳለው አጽንኦት ሰጥቷል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ባለሥልጣናት ወደፊት በትግራይ በሚያደርጉት ጉብኝት ከክልሉ መሪዎች እና የሰብአዊ እርዳታ አስፈፃሚዎች ጋር እንደሚነጋገሩም በመግለጫው ተመልክቷል። ጉብኝቱ የሚደረግበት ትክክለኛ ጊዜ ግን አልተጠቀሰም።