የትግራይ ክልል ምክር ቤት የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎትን የያዘው አወዛጋቢ አዋጅ ተግባራዊ እንዲሆን አዘዘ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ወደ ሥራ የመለሰው የትግራይ ክልል ምክር ቤት የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎትን እና በሞት የሚያስቀጡ ድንጋጌዎችን የያዘው አዋጅ ተግባራዊ እንዲሆን ትዕዛዝ አስተላለፈ።

ከስድስት ዓመት በፊት በተደረገው እና የፌደራል መንግሥት ሕገ ወጥ ባለው ምርጫ የተቋቋመው የክልሉ ምክር ቤት "የትግራይ ሕዝብ ኅልውና እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ" በሚል የወጣውን አዋጅ ያጸደቀው ግንቦት ላይ ነበር።

በህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ካቢኔ ኃላፊዎችም ስለ አዋጁ ለፍትሕ እና ፀጥታ አካላት ሥልጠና ሲሰጡ ቆይተዋል።

አዋጁ እስካሁን በክልሉ ነጋሪት ጋዜጣ ባይታተምም፤ ወደ ሥራ የተመለሰው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ምሕረት በርሀ ረቡዕ ሰኔ 17/2018 ዓ.ም. ለክልሉ ፍትሕ ቢሮ በጻፉት ደብዳቤ ሕጉ ተግባራዊ መሆን እንዲጀምር መመሪያ ሰጥተዋል። የትግራይ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የፖሊስ ኮሚሽን ግልባጭ ተጠቅሰዋል።

አፈ ጉባኤዋ በደብዳቤያቸው "በባለፈው ጉባኤያችን የጸደቀው 46 ገጽ የያዘ 'የሕዝብ ትግራይ ኅልውና እና ደኅንነት አዋጅ' በነጋሪት ጋዜጣ እስኪታተም ድረስ በጊዜያዊነት እየሠራችሁበት [እንድትቆዩ] እናሳስባለን" ብለዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ተግባራዊ እንዲሆን የወሰነው ይህ አዋጅ ከክልሉ ፖለቲከኞች እና ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ሂውማን ራይትስ ዎች ተቃውሞ ደርሶበታል። ሂውማን ራይትስ ዎች ማክሰኞ ሰኔ 16 ቀን ባወጣው መግለጫ ሕጉን "ጨቋኝ" ሲል ገልጾታል።

አዋጁ የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ሰዎችን "ለወታደራዊ አገልግሎት የሚያስገድዱበት እና ተቃዋሚዎችን ለመቅጣት" የሚያስችል "ሠፊ ሥልጣን" የሚሰጥ እንደሆነ ገልጿል።

አዋጁ "ግልፅ ያልሆነ እና እጅግ የሰፋ ቋንቋ" መጠቀሙን የገለጸው ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም፤ "ለተለያዩ ጥፋቶች እስራትን እና የሞት ቅጣትን ደንግጓል" ብሏል።

በአዋጁ ላይ እስከ ሞት ድረስ እንደሚያስቀጡ ከሰፈሩት የወንጀል ድርጊቶች አንዱ በጦርነት ጊዜ በመሠረተ ልማት፣ በሕዝብ እና በመንግሥት ተቋማት ላይ የሚደርስ ጉዳት ነው።

ከጠላት ጋር መተባበር እና የምሥጢር ማሹለክ እንዲሁም በባለሥልጣናት ወይም በትግራይ ሠራዊት ላይ ጉዳት ማድረስም እስከሞት የሚደርስ ቅጣት ያስፈርዳሉ።

በትግራይ ሠራዊት ላይ በማንኛውም መንገድ ፕሮፓጋንዳ ማካሄድ እንዲሁም የትግራይ ተወላጆችን ለጠላት መመልመል እና የትግራይ ጦር እንዲከዱ ማነሳሳትም እስከሞት ድረስ ከሚያስቀጡ ጥፋቶች መካከል ተጠቅሰዋል።

በተጨማሪም አዋጁ ዕድሜ እና ጤና የሚፈቅድለት ማንኛውም የትግራይ ተወላጅ የክልሉ መንግሥት የሚያቀርብለትን የክተት ጥሪ ተቀብሎ የመሳተፍ 'ብሔራዊ ግዴታ' እንዳለበት ደንግጓል።

ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆነ ግለሰብ ከ10,000 እስከ 50,000 ብር ተቀጥቶ ግዴታውን እንዲፈጽም እንደሚደረግም በሕጉ ተቀምጧል።

አዋጁ ወደ ኋላ ተመልሶ የትግራይ ጦርነት ከተጀመረበት ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም አንስቶ በተፈጸሙ ድርጊቶች ላይ ጭምር ተግባራዊ እንደሚሆን መገለጹም መሠረታዊ የሕግ አወጣጥ መርኅን ይጥሳል የሚል ትችት እንዲነሳበት አድርጓል።

በህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረጽዮን አማካኝነት የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት አማኑኤል አሰፋ ግን ከሰሞኑ ስለ አዋጁ በተሰጠው ሥልጠና ላይ ባደረጉት ንግግር ሕጉ ገና "በሂደት ላይ እያለ የማጠልሸት ዘመቻ" ከፍቶበታል ሲሉ ወቅሰዋል።

የአዋጁ ድንጋጌዎች መታየት ያለባቸው በመደበኛው ሁኔታ ውስጥ እንዳልሆነ የተገሩት አማኑኤል፤ "መታየት እና መተርጎም ያለበት በተጨባጭ የኅልውና አደጋ ውስጥ ያለን ሕዝብ ለማዳን ከሚደረገው ትግል አንጻር ነው" ማለታቸውን የክልሉ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

ለሁለት ዓመት በትግራይ ለተካሄደው ጦርነት ምክንያት ከነበሩ ጉዳዮች አንድ የነበረው እና ጦርነቱን ባስቆመው የፕሪቶሪያ ተቀባይነቱን ባጣው ምርጫ ተመሥርቶ የነበረውን የክልሉ ምክር ቤት ጊዜያዊ መንግሥቱን ተክቶ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በክልሉ ውጥረት ተፈጥሯል።

በህወሓት የሚመራው አስተዳደር በፌደራል መንግሥቱ የተሾሙትን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንትን ከሥልጣን ካነሳ በኋላ በክልሉ ውስጥ ሌላ ዙር ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት ነግሷል።

የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ጦርነት ለመጀመር በመዘጋጀት እየተካሰሱ ሲሆን ባለፉት ወራት በትግራይ ውስጥ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እየተካሄደ ይገኛል።