ታይታኒክን የሚያስጎበኘው ኩባንያ ሰው ሊሞት እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ነበር ተባለ

ባሕር ሰርጓጅ ብልቃጥ ጀልባ-ቲታን
የምስሉ መግለጫ, ባሕር ሰርጓጅ ብልቃጥ ጀልባ-ቲታን
ታትሟል

የታይታኒክን ቅሪት የምታስጎበኘው ቲታን የተባለችው የባሕር ሰርጓጅ ብልቃጥ የጀልባ ታክሲን የሚያስተዳድረው ኦሽንጌት ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚ ከደኅንነት ጋር በተያያዘ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ቸል ብለውታል ተባለ።

ሥራ አስፈጻሚው ስቶክተን ረሽ ከሚመለከታቸው አካላት ወደፊት ሊደርስ ስለሚችል አደጋ ቢነገራቸውም ከቁብ ሳይቆጥሩት ቆይተዋል።

ቢቢሲ እጅ የገባ የኤሌክትሮኒክ ደብዳቤ ልውውጥ እንደሚያሳየው ሰውየው ማስጠንቀቂያዎቹን ቸል ይሉ የነበረው ‘ባዶ ለቅሶ ናቸው፤ ምርምርን የሚጎትቱ ናቸው' በሚል ነበር።

ለሥራ አስፈጻሚው እንዲህ እሑድ ዕለት እንደደረሰው ዓይነት አደጋ ሊደርስ እንደሚችል ደብዳቤ ከጻፉት ሰዎች መሀል አንዱ ሮብ ማክለም ይባላሉ።

የጥልቅ ባሕር ጥናትና ምርምር መሪ ተመራማሪ ናቸው።

እርሳቸው ከአንዴም ሁለት ሦስት ጊዜ ለኦሽንጌት ሥራ አስፈጻሚ ስቶክተን ረሽ ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል ቢያሳስቡም ሥራ አስፈጻሚው ግን ግድ አልሰጡትም ተብሏል።

ቢቢሲ የተመለከታቸው የደብዳቤ ልውውጦች ይህንኑ የሚያስረዱ ናቸው።

ሮብ ማከለም ለኦሽንጌት ሥራ አስፈጻሚ ስቶክተን ረሽ ‘ደንበኞችዎን አደጋ ላይ እየጣሉ ነው፤ ይህን ባሕር ሰርጓጅ የብልቃጥ ታክሲ ከሚመለከተው አካል የደኅንነት ማረጋገጫ እስኪያገኝ ሥራውን ቢያቆሙ አጥብቄ ነው የምመክርዎ-አክባሪዎ’ ብለው ተማጽነዋል።

ሚስተር ረሽ በበኩላቸው ‘እኔ አሁንስ በዚህ ኢንዱስትሪ በደኅንነት ስም ምርምርን ለመጎተት የሚደረገው ትብተባ ነው የታከተኝ’ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ይህ በሮብ ማከለም እና በሥራ አስፈጻሚው መሀል የነበረው የደብዳቤ ልውውጥ እየጋመ ቆይቶ በመጨረሻ የኦሽንጌት ኩባንያ ጠበቆች ተመራማሪውን ማከለምን ለመክሰስ ዛቻ ሲጀምሩ ነው ነገሩ የተቋጨው።

ቢቢሲ ከተመለከታቸው የደብዳቤ ልውውጦች መካከል የሚከተሉት ሐረጎች ይገኙበታል።

“እኔ እንደሚገባኝ ራስዎንና ደንበኞችዎን ለአደጋ እየጋበዙ ነው።የታይታኒክን ስህተት እየደገሙ ይመስለኛል፤ 'መቼም አትሰምጥም ይሉ ነበር-ድሮ የታይታኒክ ሰዎች፤ እርስዎም እንዲያ እያሉ ነው”

ይህ ማስጠንቀቂያ የተጻፈው በመጋቢት 2018 ዓ/ም ነበር።

ሚስተር ረሽ ከጻፏቸው ደብዳቤዎች መሀል ደግሞ እንዲህ የሚል ይገኝበታል፡ “ሰው ልታስጨርስ ነው የሚል ሟርት ሰለቸኝ። ከእንግዲህ እንዲህ ዓይነቱን መሠረት የለሽ ማስጠንቀቂያ በኔ ላይ የተቃጣ ዛቻ አድርጌ ነው የምወስደው”

ሚስተር ረሽ እሑድ ዕለት ጥልቁ ባሕር ውስጥ በፈነዳችውና የአምስቱን ሰዎች ሕይወት በቀጠፈችው ሰርጓጅ የጀልባ ታክሲ ከተሳፈሩት ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።

ማከለም ለቢቢሲ እንደተናገሩት እርሳቸው አንድ ጊዜ ብቻ አይደለም በተደጋጋሚ ለሚስተር ረሽ ጉዟቸው ደኅንነቱ ሳይረጋገጥ ሌላ ሰው እንዳያሳፍሩ የወተወቱ ቢሆንም ማስጠንቀቂያቸው ጆሮ አላገኘም።

ወደ ጥልቅ ባሕር ሰርጓጅ ብልቃጥ የጀልባ ታክሲ መጓዝ ያለበት ተገቢውን ፍተሻና የደኅንነት ማረጋገጫ ካገኘ በኋላ መሆን ሲገባው ይህ ሳይሟላ ለንግድና ቱሪዝም ጉዞ ክፍት መሆን አልነበረበትም፤ ዋጋ አስከፍሎናል ብለዋል።

ቢቢሲ የተመለከተው አንድ ሌላ ደብዳቤ፤ “ ምንም እንኳ ምርምርና አዲስ ግኝትን የምወድ ቢሆንም ደንበኞችዎን ለአደጋ ማጋለጥዎ ኢንዱስትሪውን አዘቅት ውስጥ የሚከት ነው” ሲሉ እኚህ ተመራማሪ የሚመጣውን ተንብየው ነበር።