በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ሁለት አውሮፕላኖች አየር ላይ ተጋጭተው 2 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, POOL VIA DAILY NATION
በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ አንድ የመለማመጃ አውሮፕላን ከመንገደኞች አውሮፕላን ጋር አየር ላይ ተጋጭቶ በደረሰ አደጋ የሁለት ሰው ሕይወት አለፈ።
በሁለቱ አውሮፕላኖች ግጭት ሕይወታቸው ያለፈው በበረራ መለማመጃው አውሮፕልን ውስጥ የነበሩት የበረራ አስተማሪ እና ተማሪው መሆናቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
አውሮፕላኖቹ አየር ላይ ከተጋጩ በኋላ የበረራ መለማመጃ የሆነው አውሮፕላን በናይሮቢ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ብሔራዊ ፓርክ ወድቆ ውስጥ ወድቆ በመከስከሱ ነው ሁለቱ ሰዎች የሞቱት።
ከመለማመጃው አውሮፕላን ጋር የተጋጨው 44 ሰዎችን አሳፍሮ ተንደርድሮ ከተነሳ ንብረትነቱ ሳፋሪሊንክ ከተባለ አየር መንገድ አውሮፕላን ጋር ነው።
በግጭቱ ከባዱ አደጋ የደረሰው በመለማመጃው አውሮፕላን ላይ ሲሆን፣ መነገደኞችን አሳፍሮ የነበረው አውሮፕላን አደጋው ከተከሰተ በኋላ ተመልሶ ዊልሰን አየር ማረፊያ ለማረፍ ተገዷል።
በዚህም አደጋ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት 39 ተሳፋሪዎች እና 5 የበረራ ሠራተኞች ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰባቸው አየር መንገዱ ገልጿል።
ወደ ኬንያዋ የባሕር ጠረፋ መዳረሻ ዲያኒ ሲያቀና የነበረው የመንገደኞች አውሮፕላን አየር ላይ ሳለ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ “ከተነሳ በኋላ ከባድ ድምፅ ያለው ነገር ተሰምቷል” ብሏል አየር መንገዱ ያወጣው መግለጫ።
ናይንቲ-ናይንስ የተሰኘው የበረራ ትምህርት ቤት ንብረት የሆነችው ሴስና የመለማመጃ አውሮፕላን ከአደጋው በኋላ ከአየር ማረፊያ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ፓርክ ውስጥ ተከስክሳለች።
የኬንያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አደጋው ዛሬ ማክሰኞ ረፋድ 4፡05 ገደማ መከሰቱን ይፋ አድርጓል።
የባለሥልጣኑ የአውሮፕላን አደጋ ክፍል ከፖሊስ ጋር በመተባበር አደጋው እንዴት ሊከሰት እንደቻለ ምርመራ መጀመሩን አሳውቋል።
ዊልሰን አየር ማረፊያ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ የሚገኝ በአብዛኛው ለአገር ውስጥ በረራ ጥቅም ላይ የሚውል አየር ማረፊያ ነው።
አየር ማረፊያውን በቀን በርካታ አነስተኛ እና መካከለኛ መጠን ያላቸው አውሮፕላን ይጠቀሙበታል።
ዊልሰን አየር ማረፊያ ባለፉት ዓመታት ምንም ዓይነት አደጋ አጋጥሞት አያውቅም።












