አርሰናል ወደ ፕሪሚዬር ሊጉ አናት ሲመለስ፤ ማንቸስተር ሲቲ ለኤፍ ኤ ዋንጫ ፍፃሜ ደረሰ

ሊያንድሮ ትሮሳርድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሊያንድሮ ትሮሳርድ
ታትሟል

ከአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የተሰናበተው አርሰናል ወደ ሞሊኒው ስታድየም ተጉዞ ዎልቭስን በመርታት ወደ ፕሪሚዬር ሊጉ መሪነት ተመለሰ።

ባለፈው ሳምንት እሑድ አስቶን ቪላን በመርታታ የፔፕ ጉዋርዲዮላን ቡድን በልጦ የመገኘት ዕድላቸውን ያባከኑት መድፈኞቹ፤ ረቡዕ ዕለት በባየርን ሙኒክ ከአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ መሰናበታቸው ይታወሳል።

ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ በዎልቭስ ሜዳ ያገኙት ድል የሚኬል አርቴታን ቡድን ሞራል ከፍ የሚያደርግ ነው ተብሏል።

ምንም እንኳ በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ሊያንድሮ ትሮሳርድ ያስቆጠራት ጎል ግሩም ባትሆንም በጣም አስፈላጊ ነበረች።

አርሰናል ጨዋታውን በድንቅ ሁኔታ ቢጀምርም በጉዳት የታመሰውን ዎልቭስ ተከላካይ መስመር አልፎ መግባት ተስኖት ቆይቷል።

በሁለተኛውም አጋማሽ እንዲሁ አርሰናል ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ቢጫወትም ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ሶስት ነጥብ ለማስረገጥ ተስኖት ታይቷል።

የቡድኑ አምበል ማርቲን ኦዴጋርድ በጨዋታው መገባደጃ ያገኛት ኳስ ወደ ጎል በመቀየር ለቡድኑ አስፈላጊ ሶስት ነጥብ አረጋግጣለች።

በውጤቱ መሠረት አርሰናል ወደ ፕሪሚዬር ሊጉ ሰንጠረዥ አናት ሲመለስ አንድ ቀሪ ጨዋታ ያለው ማንቸስተር ሲቲ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በጉዳት እየታመሰ የሚገኘው ዎልቭስ ደጋፊዎች ቡድናቸውን እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ ሲግፉት አምሽተዋል።

ጃዎ ጎሜዝ እና ተቀይሮ የገባው ማሪዮ ሌሚና የአርሰናሉን ግብ ጠባቂ ዴቪድ ራያ ቢፈትኑትም ኳስን ከመረባ ማገናኘት አልቻሉም።

ከዚህ በተጨማሪ በጨዋታው ድንቅ የነበሩት የዎልቭስ አምበል ማክስ ኪልማን እና ቶቲ የተቻላቸውን ቢያደርጉም ቡድናቸውን ከሽንፈት አልታደጉትም።

በ21 ሚሊዮን ፓውንድ ባለፈው ጥር 2023 አርሰናልን የተቀላቀለው ሊያንድሮ ትሮሳርድ በአርሰናል የቋሚነት ሚና ባያገኝም በቅዳሜው ጨዋታው አስፈላጊነቱን አስመስክሯል።

በሌላ ጨዋታ በኤፍ ኤ ግማሽ ፍፃሜ የተገናኙት ማንቸስተር ሲቲ እና ቼልሲ በዌምብሊ ስታድየም ያደረጉት ፍልሚያ በሲቲ አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሳምንቱ አጋማሽ በቻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ በሜዳው በሪያል ማድሪግ ከውድድሩ ውጭ የሆነው ማንቸስተር ሲቲ ከሽንፈቱ አገግሞ ለኤፍ ኤ ዋንጫ ፍፃሜ ደርሷል።

በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የፍፁም ቅጣት ምት የሳተው ፖርቹጋላዊው በርናርዶ ሲልቫ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ጎል በማስቆጠር ስሙን አድሷል።

የቼልሲው አጥቂ ኒኮላስ ጃክሰን በርካታ የጎል ዕድሎችን ቢያገኝም ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል። በካራባዎ ዋንጫ ፍፃሜ ከሊቨርፑል ተገናኝተው በርካታ ዕድሎችን ያባከኑት ቼልሲዎች ከስህተታቸው የተማሩ አይመስሉም።

በሁለተኛው አጋማሽ የቼልሲው ኮል ፓልመር የመታት የቅጣት ምት ኳስ በፍፁም ቅጣት ምት ሳጥኑ ውስጥ የነበረውን የጃክ ግሪሊሽ እጅ ብትነካም ቼልሲ ፍፁም ቅጣት ምት አለማግኘቱ ብዙዎችን አስቆጥቷል።

ማንቸስተር ሲቲ የፕሪሚዬር ሊጉን እና የኤፍ ኤ ዋንጫውን በማንሳት በተከታታይ ሁለት ዋና ዋና ዋንጫዎችን ለማንሳት የሚያደርገውን ጥረት ይቀጥላል።

ምንም እንኳ የፔፕ ጉዋርዲዮላ ቡደን በተደጋጋሚ ድካም እና መጫጫን የታየባቸው ቢሆንም የኋላ ኋላ ውጤት ማግኘት ችለዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ አንድ ዒላማውን የጠበቀ ኳስ ወደ ቼልሲ ጎል ያልሰነዘሩት ሲቲዎች በበርናርዶ ሲልቫ የ84ኛ ደቂቃ ጎል ወደ ፍፃሜው አምርተዋል።

በሌላ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ ከሰዓት ማንቸስተር ዩናይትድ ከኮቨንትሪ በዌምብሊ ስታድዬም ይጫወታሉ።