አርሴናል ከማንቸስተር ሲቲ: የሳምንቱን ተጠባቂ ጨዋታ፣ ማን ያሸንፋል?

ባለፈው ዓመት ለዋንጫ ሲፎካከሩ የነበሩት አርሴናል እና ማንቸስተር ሲቲ እሑድ የሚያደርጉት ጨዋታ በእጅጉ ተጠባቂ ነው።
መድፈኞቹ የገጠማቸው የተጨዋቾች ጉዳት ያሰጋቸው ይሆን?
ቡካዮ ሳካ የማይሰለፍ ከሆነ ለአርሴናል እንደሚያሰጋ የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን ይገልጻል።
ስምንተኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሑድ ይከናወናሉ።
የእነዚህን ጨዋታዎች ግምት ክሪስ ሱተን እንደሚከተለው አስቀምጧል።
ቅዳሜ
ሉተን ከ ቶተንሃም
ሉተን ባለፈው ሳምንት ኤቨርተን ላይ ካስመዘገበው ድል በኋላ በሳምንቱ አጋማሽ በበርንሌይ መሸነፉ ጉዞውን ገትቶታል።
ባያሸንፉ እንኳን አቻ መውጣት ያለመሸነፍ ጉዟቸውን ወደ ሦስት ጨዋታ ያሳድገው ነበር።
ጥሩ በመጫወት ላይ ከሚገኙት ቶተንሃሞች ነጥብ የማግኘት ዕድላቸው አነስተኛ ነው።
ቶተንሃም በጠንካራ ጉዞው ይቀጥላል።
ግምት፡ 1 – 3

በርንሌይ ከ ቼልሲ
ሁለቱም ቡድኖች ያስመዘገቡትን ውጤት ማጠናከሪያ ጨዋታቸው ቢሆንም ለመገመት ግን ከባድ ነው።
ቼልሲ ከነሐሴ በኋላ ያስመዘገበውን ድል ለማስቀጠል የሚጥርበት ጨዋታ ነው።
በርንሌይም ከአስቸጋሪ አጀማመር በኋላ ባለፈው ሳምንት ሉተንን አሸንፏል።
በርንሌዮች በሜዳቸው ሁሉንም ጨዋታዎች የተሸነፉ ሲሆን፣ ይህን ጨዋታ በአቻ ውጤት እንደሚያጠናቅቁ እገምታለሁ።
ግምት፡ 1 – 1
ኤቨርተን ከ በርንመዝ
በርንመዝ ዘንድሮ አስቸጋሪ ጉዞ እያደረገ ይገኛል።
ዶምኒክ ሶላንኬ ጎሎችን እያስቆጠረ ቢሆንም ቡድኑ ለማጥቃት ዝግጁ ስለመሆኑ እጠራጠራለሁ።
ኤቨርተንም ጥሩ ጉዞ እያደረገ ባይሆንም ከሉተን ሽንፈት በኋላ ውጤት ለማስመዝገብ የሚሞክርበት ጨዋታ ነው።
በጉዲሰን ፓርክ አራት ጨዋታዎችን ከተሸነፉ በኋላም ወደ ድል የሚመለሱበት ሳምንት ነው።
ግምት፡ 1 – 0
ፉልሃም ከ ሼፊልድ ዩናይትድ
ሼፊልድ ዩናይትድ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል።
ከዚህ ጨዋታም እንዴት ውጤት እንደሚያስመዘግቡ አላውቅም።
ፉልሃም ዘንድሮ በውጣ ውረድ ውስጥ እያለፈ ቢሆንም በዚህ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ያሳካል።
ግምት፡ 1 – 0

ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ብሬንትፎርድ
ዩናይትድ በሜዳው በክሪስታል ፓላስ እና በጋላታሳራይ ተከታታይ ሽንፈት አስተናግዷል።
አጥቂው ራስመስ ሆይሉን ለደጋፊዎቹ ተስፋ ቢፈጥርም በግብ ጠባቂው አንድሬ ኦናና ግን ደስተኛ አይደለሁም።
ብሬንትፎርድ ባለፉት ሳምንታት ውጤታማ ባይሆንም የተደራጁ እና በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት የሚመርጡ ይመስለኛል።
ዩናይትድ ጎል ማስተናገዱ አይቀርም። እንደ ሆይሉን ያሉ ተጫዋቾች ግን ልዩነት ፈጣሪ ይሆናሉ።
ግምት፡ 2 – 1
ክሪስታል ፓላስ ከ ኖቲንግሃም ፎረስት
ሁለቱንም ቡድኖች ለማሸነፍ አስቸጋሪዎች ሲሆኑም ግቦችን በማስቆጠር ረገድ ግን ጥያቄ ይነሳባቸዋል።
ክሪስታል ፓላሶች የኤበረቺ ኤዜን አገልግሎት በጉዳት ምክንያት አያገኙም። ካለእሱ ደግሞ የማሸነፍ ዕድላቸው አነስተኛ ነው።
ግምት፡ 1 – 1

እሑድ
ብራይተን ከ ሊቨርፑል
ሊቨርፑሎች ባለፈው ሳምንት ከቶተንሃም ጋር በነበራቸው ጨዋታ የሉዊስ ዲያዝ ጎል በመሻሩ ዕድለኞች አልነበሩም። ሁለት ተጫዋቾቻቸው በቀይ ከሜዳ በመባረራቸው ግን የተወሰነ ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው።
ብራይተኖች በአውሮፓ መድርክ ያደረጉት ጨዋታ ምን ያህል ተጽዕኖ እንደፈጠረባቸው የሚታይ ይሆናል።
ባለፈው ከአውሮፓ መድረክ መልስ በርንመዝን ቢያሽንፍም የእሁዱ ጨዋታ ግን የተለየ ይሆናል።
ብራይተን ባለፈው ዓመት አሜክስ ስታዲየም ላይ ሁለት ጊዜ ቀያዮቹን ማሸነፍ ችሏል። የአሁኑ ሊቨርፑል ግን በተለይም የተለየ አማካይ ያለው ነው።
ግምት፡ 2 – 3
ዌስት ሃም ከ ኒውካስል
ኒውካስል ረቡዕ ዕለት ፒኤስጂ ላይ ያስመዘገበው ድል ትልቅ ሲሆን በጠንካራ ጉዞም ላይ ይገኛሉ።
ኒውካስልም ሐሙስ ምሽት በአውሮፓ መድረክ በመሳተፉ ለዚህ ጨዋታ እንዴት እንደሚቀርቡ የሚታይ ይሆናል።
ዌስት ሃሞች ጥሩ አጀማመር ያደረጉ ሲሆን፣ በደረጃ ሰንጠረዡም ከኒውካስል በላይ ተቀምጠዋል። በዚህ ምክንያት ጨዋታው ተቀራራቢ ቢመስልም በጥሩ አቋም ላይ ወደሚገኘው ቡድን አደላለሁ።
ግምት፡ 1 – 2
ዎልቭስ ከ አስቶን ቪላ
አስቶን ቪላ በድንቅ ጉዞ ላይ ሲሆን፣ ዎልቭስ ደግሞ ማንቸስተር ሲቲን በማሸነፍ አስገራሚ ውጤት አስመዝግቧል።
ሁለቱም ቡድኖች ተደራጅተው ስለሚጫወቱ በርካታ ጎል የሚቆጠርበት ጨዋታ አይሆንም።
ቪላ እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ። አጥቂው ኦሊ ዋትኪንስ ጎል ቢያስቆጥር አይገርመኝም።
ግምት፡ 0 – 2
አርሴናል ከ ማንቸስተር ሲቲ
አርሴናል ከጋብርኤል ማርቲኔሊ እና ቡካዮ ሳካ ውጭም ጠንካራ ቡድን ነው። ሁለቱ ተጫዋቾች በሙሉ ብቃት በዚህ ጨዋታ ቢሰለፉ ግን የበለጠ ዕድል ይኖረው ነበር።
የሲቲ ቡድንም በሚያኮራ ደረጃ ላይ አይደለም። ኤርሊንግ ሃላንድም ባለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ጎል ብቻ ቢያስቆጥርም አሁንም ግን አደገኛ ተጫዋች ነው።
ሲቲ ጥሩ ባይጫወትም አርሴናልን እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ።
ባለፈው ሳምንት ሁለት ጨዋታዎችን የተሸነፉ ቢሆኑም፣ በዚህ የውድድር ወቅት ግን በርካታ ሽንፈቶች ይገጥሟቸዋል ብዬ አልጠብቅም።
ግምት፡ 1 – 2












