በናይጄሪያ ሰባት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በጄኔሬተር ጭስ ታፍነው ሕይወታቸው አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጄሪያ ቢያንስ ሰባት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በጄኔሬተር ጭስ ታፍነው መሞታቸው ተገለጸ።
በነዳጅ በበለፀገችው የናይጄሪያዋ ባይልሳ ግዛት በሚገኝ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ባለ የሙዚቃ ስቱድዮ ሳሉ ነው ተማሪዎቹ ከጄኔሬተር በሚወታ ጭስ ታፍነው ሕይወታቸው ያለፈው።
ወጣቶቹ ወንዶች ሰኞ እስከ ምሽት ድረስ ሠርተው ስቱድዮውን ቆልፈው ተኝረው ነበር። ጄኔሬተሩን ሳያጠፉት እንደተኙም ተገልጿል።
የፖሊስ ምርመራ እየተካሄደ ቢሆንም ከጄኔሬቴሩ በሚወጣ ካርቦን ሞኖክሳይድ ጭስ ሳይታፈኑ እንዳልቀረ ተገልጿል።
በናይጄሪያ ባለው የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ምክንያት ብዙዎች በነዳጅ የሚሠራ ጄኔሬተር ይጠቀማሉ።
ትናንት ማክሰኞ ምሽት ስድስት አስክሬኖች የተገኙ ሲሆን፣ አንድ ተማሪ ሳይሞት ራሱን ስቶ ተገኝቶ የነበረ ቢሆንም፣ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ ሕይወቱ ማለፉን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በስቱዲዮው መስኮት የሰዎች ሰውነት ከተመለከቱ በኋላ ባደረጉት ጥቆማ ነው የተማሪዎቹ አስክሬን የተገኘው።
ፖሊስ በቦታው ደርሶ አስከሬናቸውን ከነበሩበት ስቱዲዮ ውስጥ አውጥቷል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ሙሳ መሐመድ ለቢቢሲ በተማሪዎቹ ሕልፈት ዙሪያ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
“ከጄኔሬተሩ የወጣው ጭስ በፈጠረው ካርቦን ሞኖክሳይድ ታፍነው እንደሞቱ ይታመናል። ምርመራ እየተካሄደ ነው” ብለዋል።
ሟቾቹ የናይጀር ዴልታ ዩኒቨርሰቲ ተማሪዎች ናቸው። ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በሙዚቃ ሥራ ውስጥም ይሳተፉ ነበሩ።
በአፍሪካ በነዳጅ ሀብት በምትታወቀው ናይጄሪያ ከጄኔሬተር በወጣ ጭስ ሰዎች ታፍነው ሲሞቱ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
በናይጄሪያ ኢሞ ግዛት፣ እአአ በ2009 ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 13 የአንድ ቤተሰብ አባላት በጄኔሬተር ጭስ ታፍነው መሞታቸው ይታወሳል።
ኢንተርናሽናል ኢነርጂ ኤጀንሲ እንዳለው፣ ናይጄሪያውያን ለሚያስፈልጋቸው 40 በመቶ የኃይል አቅርቦት ጄኔሬተር ይጠቀማሉ።
ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት ለተሽከርካሪዎች እና ሌሎችም በጄነሬተር ለሚሠሩ መገልገያዎች የተፈጥሮ ጋዝ እንዲጠቀሙ መመሪያ አውጥተዋል።
ይህም የነዳጅ ዋጋን ለመቀነስ እና ንጹህ የኃይል ምንጭ ለመዘርጋት ነው።












