ሊቨርፑል በሜዳው ቼልሲን ሲረታ ድል የቀናው ማንቸስተር ሲቲ ሁለተኛ ደረጃን ከአርሰናል ተረክቧል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወጣቱ ኮነር ብራድሊ ለሊቨርፑል የመጀመሪያ ጎሉን በማስቆጠር ታሪክ በሠራበት ምሽት ቀያዮቹ ቼልሲን አሸንፈዋል።
ቼልሲን 4-1 የሩታው የየርገን ክሎፕ ቡድን ሊጉን በአምስት ነጥብ ልዩነት እየመራ ይገኛል።
ረቡዕ ምሽት ሶስት ነጥብ ያገኘው ሲቲ እና ከትናንት በስትያ ድል የቀናው አርሰናል ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ሊቨርፑል የበላይነቱን በወሰደበት የረቡዕ ምሽት ጨዋታ ዳርዊን ኑኔዝ አራት ጊዜ የግቡን አግዳሚ እና ቋሚ መትቷል።
ለሊቨርፑል የመጀመሪያዋን ጎል ያስቆጠረው ፖርቹጋላዊው አጥቂ ዲየጎ ጆታ ነው።
የ20 ዓመቱ ሰሜን አየርላንዳዊው ተጫዋች ኮነር ብራድሊ ደምቆ ያመሸ ሲሆን ሁለት ጎሎች ከማስቆጠሩም በላይ ሁለት ለጎል የሚሆኑ ኳሶች አመቻችቶ አቀብሏል።
ሃንጋሪያዊው ዶሚኒክ ስቦዝላይ እና ኮለምቢያዊው ዲያዝ ሁለቱን ተጨማሪ ጎሎች አክለው አንፊልድ እንዲፈነድቅ አስችለዋል።
ሊቨርፑል እና ቼልሲ በካራባዎ ዋንጫ ፍፃሜ በአውሮፓውያኑ የካቲት 25 በግዙፉ ዌምብሊ ስታድየም ይገናኛሉ።
የርገን ክሎፕ በውድድር ዘመኑ መገባደጃ ቡድኑን እንደሚለቁ ካሳወቁ በኋላ ይህ ሁለተኛ ጨዋታቸው ነው።
ሊቨርፑል ባለፈው እሑድ በኤፍ ኤ ዋንጫ ፍልሚያ ኖርዊችን 5-2 መርታቱ ይታወሳል።
ቼልሲ በሜዳው ካለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ ሽንፈት አስተናግዶ አያውቅም።
ነገር ግን ከሜዳቸው ውጭ በሚያደርጓቸው ደካማ ውጤት ነው ያላቸው። ከሜዳቸው ውጭ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ከስድስቱ አምስቱን ተረትተው ነው ወደ አንፊልድ የመጡት።
በሌላ ጨዋታ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው በርንሊን አስተናግዶ 3-1 አሸንፏል።
ጁሊያን አልቫሬዝ ሁለት ጎሎች ሲያስቆጥር ሮድሪ አንድ በማከል ሲቲ አርሰናል ገልብጦ ሁለተኛ ደረጃን እንዲጎናፀፍ አስችለውታል።
ሲቲ ከመሪው ሊቨርፑል በአምስት ነጥብ ዝቅ ብለው ቢገኙም አንድ ቀሪ ጨዋታ አላቸው።
ሌላኛው ረቡዕ ምሽት የተደረገው ፍልሚያ ቶተንሀም ከብሬንትፈርድ በስፐርስ ስታድየም ያደረጉት ነው።
አምስት ጎሎች በታዩበት ጨዋታው ባለሜዳው ቶተንሀም 3-2 በመርታት ወደ አራተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።
ብሬንትፈርድ 1-0 እየመሩ ለእረፍት ወደመልበሻ ክፍል ቢያመሩም በሁለተኛው አጋማሽ ቶተንሀም በስምንት ደቂቃ 3 ጎሎች በማስቆጠር የጨዋታውን ሚዛን ቀይሯል።
ኡዶጊ፣ ጆንሰን እና ሪቻርልሰን ለቶተንሀም ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ኒል ሞፔ እና አይቫን ቶኒ ለብሬንትፈርድ አስቆጥረዋል።
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዛሬም የሚቀጥል ሲሆን ሐሙስ ምሽት ዌስት ሀም ከቦርንመዝ፤ ዎልቭስ ከማንቸስተር ዩናይትድ ይፋለማሉ።












