ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የደቡብ አፍሪካን ጀግና የገደለው የቀኝ አክራሪ ጽንፈኛ ጃኑስ ዋሉስ ከአገር ሊባረር ነው
በደቡብ አፍሪካ የፀረ አፓርታይድ ጀግና በመባል የሚታወቀውን ክሪስ ሃኒን በመግደል ወንጀል ተከስሶ የተፈረደበት የቀኝ አክራሪ ጽንፈኛው ጃኑስ ዋሉስ ወደ ትውልድ አገሩ ፖላንድ ሊወሰድ ነው ሲል መንግሥት አስታወቀ።
የ71 ዓመቱ ጃኑስ ዋሉስ በአውሮፓውያኑ 1993 ደቡብ አፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለያዩ የአገሪቱ ተወላጆችን ያሳተፈ ምርጫ ለማካሄድ በምታዘጋጅበት ወቅት ሃኒን ከቤቱ ውጭ በጥይት ገድሎታል።
እ.ኤ.አ. በ2022 በይቅርታ ከእስር ከመፈታቱ በፊት ለሶስት አስርት ዓመታት ያህል በደቡብ አፍሪካ እስር ቤት አሳልፏል።
አሁንም ከዘረኝነት እና ከአፓርታይድ ውርስ ጋር እየታገለ ባለችው ደቡብ አፍሪካ ይህ ከፍተኛ ተቃውሞ እና ቅራኔ አስነስቷል።
ዋሉስ አርብ ምሽት ደቡብ አፍሪካን ለቅቆ እንደሚወጣ እና የፖላንድ መንግሥት ወጪውን እንደሚሸፍን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዮን ሽሪበር ተናግረዋል።
ውሳኔውን መንግሥት የወሰነው አለመሆኑን እና በሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት የተላለፈውን ውሳኔ እያከበሩ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
ሽሪበር በኤክስ ገጻቸው ላይ፣ ለደቡብ አፍሪካውያን የአፓርታይድን "የጨለማ ጊዜ" የሚያስታውስ "ልብ ሰባሪ ቀን" ሲሉ አስፍረዋል።
የሃኒ ባለቤት፣ ሊምፎ ሃኒ፣ መንግሥት እና የደቡብ አፍሪካ ኮሚኒስት ፓርቲ በመጨረሻው ሰዓት ውሳኔውን ስላሳወቋት ማዘኗን ተናግራለች።
አክላም ሐሙስ ዕለት የዋሉስ መፈታት ብቻ እንደተነገራት ገልጻለች።
ሃኒ የነጮች አገዛዝን በመቃወም ከፊት የሆነው እና በስልጣን ላይ ያለው የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ቁልፍ አባል እንዲሁም የደቡብ አፍሪካ ኮሚኒስት ፓርቲ መሪ ነበር። ከተገደለበት ጊዜ ጀምሮ ለአገሪቱ ነፃነትና እኩልነት በተደረገው ትግል መስዋዕት የሆነ የተከበረ ጀግና ሆኗል።
ኤኤንሲ በሃኒ መገደል ምክንያት የተከሰተውን ሕመም አስታውሶ፣ ገዳዩ ከእስር መፈታቱ "አባታችንን እና ጓዳችንን የገደለችው ጥይት በእኛም ልብ ውስጥ የማለፏ" ማስታወሻ ነው ብሏል።
" ለሰብአዊነት፣ ለዲሞክራሲ እና ለፍትህ ነፃነትና ፍቅር የመጨረሻውን ዋጋ የከፈለው የሰማዕት እና የነጻነት ታጋዩ ደም ከእጁ ይንጠባጠባል።" ሲልም ያክላል።
ዋሉስ በ1981 ከፖላንድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተዛውሮ ዜግነት የተሰጠው ሲሆን፣ የግድያ ወንጀሉን ከፈጸመ በኋላ ተነጥቋል።
መጀመሪያ ላይ ከግብር አበሩ ክላይቭ ደርቢ-ሌዊስ ጋር የሞት ፍርድ ተፈረዶበት የነበረ ሲሆን፣ ደቡብ አፍሪካ የሞት ቅጣትን ከሰረዘች በኋላ ቅጣቱ ወደ እድሜ ልክ እስራት ተቀየሯል።
እ.ኤ.አ. በ 1997 ለእውነት እና እርቅ ኮሚሽኑ ፍርድ ቤት "አገሪቷን ወደ ምስቅልቅል ሁኔታ እንድትገባ እና ቀኝ ዘመሞች ስልጣንን እንዲቆጣጠሩ የሚፈቅድ" ድርጊት ፈጽሟል በሚል ሃኒን መግደሉን ተናግሯል።
ዋሉስ በኮሚኒስቷ ፖላንድ ዘመን ያጋጠመው ሃኒን ለመግደል በወሰነው ውሳኔ ላይ አስተዋጽኦ አድርጓል ብሎ ነበር።
ደቡብ አፍሪካ የነጭ የበላይነትን ያሰፈነው የአፓርታይድ ሥርዓት ሊያከትም በተቃረበበት በዚያ ወቅት በከፍተኛ ስጋት ተወጥራ ነበር
የኤኤንሲ መሪ የነበሩት ኔልሰን ማንዴላ እ.ኤ.አ. በ1990 ከእስር የተፈቱ ሲሆን፣ የነጮች የበላይነት እንዴት እንደሚያበቃ እና ምርጫ ሊደረግ እንደሚችል ከአፓርታይድ መሪዎች ጋር በሚነጋገሩበት ወቅት፣ የተወሰኑ ነጮች የሕግና ሥርዓት ጥሰት ተፈጥሮ አለመረጋጋት ይኖራል የሚል ስጋት ገብቷቸው ነበር።
ብዙዎች የሃኒ መገደል የዘር ፍጅት ያስጀምራል ብለው ፈርተው ነበር።
አንዳንዶች ደቡብ አፍሪካ በቀጣዩ ዓመት ወደ ዴሞክራሲ የምታደርገውን ሽግግር ሊያደናቅፈው ተቃርቦ ነበር ይላሉ።
የኤኤንሲ ዋና ፀሃፊ ፊኪሌ ምባሉላ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የዋሉስ ግድያ "ደቡብ አፍሪካን ከታላላቅ መሪዎቿ አንዷን አሳጣ" ብለዋል።
"ድርጊቱንና ሴራውን ሙሉ በሙሉ ሳይናዘዝ ከአገር መባረሩ ኢፍትሃዊ ነው" ሲል አክለዋል።
ምባሉላ "የወንጀሉን አጠቃላይ ስፋት ለማጋለጥ" ግድያው ላይ አጠቃላይ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል። የደቡብ አፍሪካ ኮሙኒስት ፓርቲም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥቷል።
ዋሉስ በፖላንድ ባሉ የቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች ዘንድ ታዋቂ ሰው ሆኗል።
ምስሉ በአንገት ልብስ፣ ቲሸርት እና ፖስተሮች ላይ ታትሟል። እነዚህ ምርቶች በደቡብ አፍሪካ ሳይቀር ተሽጠዋል።
ዋሉስን ለመጽሐፍ በሚል ቃለ መጠይቅ ያደረገለት ጋዜጠኛ በአገሪቱ ያሉ ጽንፈኞች "የነጮች ዘር ታላቅ ተስፋ" አድርገው ይመለከቱት እንደነበር ተናግሯል።
ዋሉስ ሃኒን በመግደሉ አንድም ጊዜ መጸጸቱን ገልጾ አያውቅም።