የሶማሊያ ድርቅ፡ ቤተሰቡን ከረሃብ ለመታደግ የሚታገለው ታዳጊ

ዳሂር

የፎቶው ባለመብት, BBC/ ED HABERSHON

ታትሟል

ዳሂር ወንድሙን በረሃብ አጥቷል። አሁን ሁለት እህቶቹ ከበሽታንና ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ጋር ግብ ግብ ላይ ናቸው።  የቢቢሲው ጋዜጠኛ አንድሪው ሃርዲንግ በ40 ዓመታት የሶማሊያ ታሪክ ታይቶ የማያውቀው አስከፊ ድርቅ ለመሸሽ የተገደደውን ቤተሰብ ለመጎብኘት ወደ ባይደዋ አቅንቷል።

ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ አንዳንድ አንባቢዎች ሊያሳዝኑ የሚችሉ ምስሎችን ይዟል።

የአስራ አንድ ዓመቱ ዳሂር በባይዶዋ ወጣ ብሎ ወደሚገኘው ትምህርት ቤቱ እየሄደ ነው። ብቸኛ ሸሚዙንና ሱሪውን ለብሷል። ቀሪ ንብረቱ አዲሱ የትምህርት መጽሐፉ ነው።

የትምህርት ቤቱ ብቸኛ መምህር አብዱላህ አህመድ ይባላል። 29 ዓመቱ ነው። የሳምንቱን ቀናት በእንግሊዘኛ በጥቁር ሰሌዳ ላይ ይጽፋል። ዳህርና 50 የሚደርሱ የክፍል ጓደኞቹ “ሳተርዴይ፣ ሰንዴይ፣ መንዴይ...” ይላሉ።

የተማሪዎቹ ፍላጎት ለተወሰኑ ደቂቃዎች ከፍ ይላል። ወዲያው ደግሞ ማዛጋት እና ማሳል እንደገና ይጀምራሉ።

"ከእነዚህ ልጆች ቢያንስ 30 ያህሉ ቁርስ የበሉ አይመስለኝም። አንዳንድ ጊዜ መጥተው እንደራባቸው ይነግሩኛል። ትምህርታቸው ላይ ማተኮር ወይም ለመምጣትም ይቸግራሉ" ይላል መምህር አህመድ።

ከስድስት ሳምንታት በፊት ይህንን የደቡብ ሶማሊያን ክፍል ጎበኝተን ነበር። ከቀለሱት አነስተኛ ጎጆ ቤት ደጃፍ ዳሂር ከእናቱ ፋጡማ ጎን ተቀምጦ እያለቀሰ ነበር።

ከቀናት በፊት ታናሽ ወንድሙ ሰላት በድርቅ ከተጠቃው ገጠራማ አካባቢ ወደ ባይደዋ ሲጓዝ በረሃብ ህይወቱ አለፈ።

ሰላት የተቀበረው ጥቂት ሜትሮች ራቅ ብሎነው። መቃብሩ በአዲስ መጤዎች በተገነቡ ጎጆዎች ተከቧል።

"ስለ እህቶቼ እጨነቃለሁ። አጥባቸዋለሁ። ፊታቸውንም አጥባለሁ" ሲል ዳሂር የስድስት ዓመቷን እህቱ መሪያምን እያየ ይናገራል። መሪያም ከባድ ሳል አለባት። ራስ ምታት እንዳለባትም ትገልጻለች። የአራት ዓመቷ ማልዩን በጭንቀት ተውጣ እናቷ ጉልበት ስር አረፍ ብላለች።

የትምህርት ክፍል

የፎቶው ባለመብት, BBC/ ED HABERSHON

ፋጡማ እጇን ልጇ ግንባር ላይ አስቀምጣ "አተኩሳለች። ኩፍኝ ያለባት ይመስለኛል። ሁለቱም ኩፍኝ ያለባቸው ይመስለኛል።" ትላለች።

በቅርብ ወራት ኩፍኝ እና የሳምባ ምች በባይዶዋ ከተማ ተስፋፍቷል። በሽታን የመከላከል አቅማቸው የተዳከሙ በርካታ ህፃናትም ህይወታቸው አልፏል።

መሃል ባይዶዋ በሚገኘው ሆስፒታል ያሉ ዶክተሮች እና ነርሶች ለጨቅላ ሕፃናት ህክምና ለመስጠት ላይ ታች እያሉ ነው።

ብዙ የልጆች እግር ጠቁሯል። በከባድ ቃጠሎ የተነሳ የሚመስል ቁስለትም ለረዥም ጊዜ በቆየው ረሃብ ምክንያት ተከስቶባቸዋል።

የሆስፒታሉ ዋና ዶክተር አብዱላሂ ዩሱፍ "ተጨማሪ [የእርዳታ] አቅርቦቶችን አግኝተናል። ግን በቂ አይደለም" ብለዋል።

ፋጡማ ከልጆቿ ጋር

የፎቶው ባለመብት, BBC/ ED HABERSHON

የምስሉ መግለጫ, ፋጡማ ከልጆቿ ጋር

"ዓለም ለሶማሊያ ድርቅ አሁን ትኩረት ሰጥቷል። ከዓለም አቀፍ ለጋሾች የሚመጡ ጎብኚዎችን እናያለን። ይህ ማለት ግን በቂ ድጋፍ እያገኘን ነው ማለት አይደለም። በቅርቡ ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ነው ያለው።"

ከስድስት ሳምንታት በፊት የነበረውን ሁኔታ “አስፈሪ” ሲሉ ይገልጹታል። ዛሬ ለህክምና የሚመጡ ህጻናት መጠነኛ መቀነስ ማስመዝገቡን ያምናሉ።

ይህ ግን ለጥቂት ቀናት በነበረው ዝናብ ምክንያት ይሆናል ይላል። ልጆቻቸውን ወደ ህክምና ከማምጣት አንዳንዶች በዝናቡ ምክንያት መንገድ ተበላሽቶባቸው ሌሎች ደግሞ ሰብል ለመዝራት ቀርተዋል በሚል ነው።

ሁኔታው እየተባባሰ ነው

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወደ ካምፑ እንመለስ። ፋጡማ በጋራ ከሚጠቀሙበት ቧንቧ ውሃ ቀድታ ተመልሳለች። የታመሙ ሴት ልጆቿ በዳሱ ውስጥ ተዳክመው ተኝተዋል። ዳሂር ሳህን በማጠብ ሊረዳት ከጎጆው ወጣ።

ፋጡማ "ልጄ ያግዘኛል። ሴቶቹን ልጆችን ለመርዳት ብዙ ይሠራል" ትላለች።

ውሃ ስታፈላ ስልኳ መጥራት ጀመረ። የ60 ዓመቱ ባለቤቷ አዳን ኑር በእግር ጉዞ ሦስት ቀናት ከሚፈጀው መንደራቸው ነበር የሚደውለው። አካባቢው በእስላማዊው ታጣቂ ቡድን አልሸባብ ቁጥጥር ስር ይገኛል።

"ማሽላ ዘርቻለሁ። ደህና ነው። በቅርቡ ይመለሳል። ከብቶቻችንን ግን አጥተናል። በአዝመራው ብቻ መተዳደር የምንችልበት መንገድ ስለሌለ እዚሁ እቆያለሁ። ያኛው የህይወት መንገድ አብቅቷል" ትላለች ፋጡማ ስልኩን ከዘጋች በኋላ።

የውሳኔዋ በብዙ ባለሙያዎች ይደገፋል። ይህ የዝናብ ወቅት ልክ እንዳለፉት አራት የዝናብ ወቅቶች የማይዘልቅ ሲሆን በቀውሱ ላይም ምንም አይነት አዎንታዊ ተጽዕኖ አላሳደረም።

"አሁንም እየተባባሰ ነው። ብዙ ሰዎች አሁንም ምግብ፣ ውሃ እና ደኅንነት ፍለጋ ወደዚህ እየመጡ ነው። ብዙ ህጻናት በምግብ እጦት እየሞቱ ነው። [መንግሥት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ] ሁኔታውን እንደ ረሃብ እንዲቆጥሩት እናሳስባለን” ሲሉ የባይዶዋ ከንቲባ አብዱላህ ዋቲን ተናግረዋል።

ተፈናቃዮቹን አንድ የጦር ጄኔራል ከአልሸባብ የሚደርሰው ስጋት እየጨመረ ስለመጣ ሰዎች ከፈንጂዎችን እና ጥቃቶችን ራሳቸውን እንዲጠብቁ አስጠንቅቀዋል።

የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች እና ሚሊሻዎች በሰሜን በኩል ያገኙትን አነስተኛ ድል ያሰፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ግን በድርቅ በጣም የተጎዱ አንዳንድ የገጠር ማህበረሰቦችን ለመድረስ መንገዱን የበለጠ ከባድ ያደርገዋል።

ፋጡማ ሁለቱን በጣም የታመሙ ልጆቿን ከጎጇቸው ወለል ላይ ብርድ ልብስ አንጥፋ አስቀምጣቸዋለች።

ህጻናቱን ወደ ሆስፒታል ለመውሰድ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለባህላዊ ህክምና ዕድል ሰጥታለች። ድካም የተጫናት ፋጡማም ከሴቶቹ ጎን አረፍ አለች።

ዳሂር በተቀመጠበት ሆኖ እየተመለከተ ደጋግሞ “እንዲሻላቸው ብቻ ነው የምፈልገው” አለ።