ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ከባድ ፈተና የተጋረጠበት የአዲሱ የኒው ዮርክ ከንቲባ የሥልጣን ዘመን

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ማምዳኒን ለመጣል ከናታንያሁ እስከ ትራምፕ፣ ከኤለን መስክ እስከ ሪፐብሊካን ፓርቲ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም።

በመጨረሻ ግን የጭቁን ኒው ዮርካዊያን ሕዝብ ድምፅ አሸነፈ።

ዞህራን ማምዳኒ እንዴት አሸነፈ? የሚለው ራሱን የቻለ የዶክትሬት ዲግሪ ጥናት ይወጣዋል።

በደምሳሳው ግን ዕድሜው፣ ንቃቱ እና ለሕዝብ ቅርብ መሆኑ ተወዳጅ አድርገውታል።

በምረጡኝ ዘመቻ ወቅት እሱ ዲጂታል ተፎካካሪዎቹ አናሎግ ሆነው ነው የተወዳደሩት።

ነገረ ሥራው ለዘመኑ ትውልድ የሚስማማ ነው። ሲናገር ከአፉ ማር ጠብ ይላል የሚባልለት ዓይነት ነው።

በወጣትነቱ በራፕ ሙዚቃ እስክስ ቅንጥስ ብሏል። ለነገሩ አሁንም ወጣት ነው።

ታላቋን የአሜሪካ ከተማ ከንቲባነት ያሸነፈበት የድል ደግስ ላይም እንደመደነስ እየቃጣው ነበር።

በኒው ዮርክ ጎዳናዎች እየዞረ የጀብሎ ነጋዴ ሳይቀር እያስቆመ አቅፎ ይስማል። ጆሮ ሰጥቶ ይሰማል። የቢጫ ታክሲ ሾፌሮችን ጊዜ ሰጥቶ ምሬታቸውን ያዳምጣል።

የሕዝብ ልጅ መሆኑን ከአንድም ሁለት ሦስት ጊዜ አስመስክሯል።

ተፎካካሪዎቹ በዕድሜ ወላጆቹ ይሆናሉ።

እሱ ገና 35 አልደፈነም። የወቅቱ የኒው ዮርክ ከንቲባ አንድሩ ኩሞ የማምዳኒ ዕድሜ እጥፍ ናቸው። እሱን ለማሸነፍ ፓርቲ ሳይቀር ቀያይረዋል። መጀመርያ ዲሞክራት ነበሩ። ቀጥሎ በግል ተወዳደሩ አልቻሉትም።

ሌላው ተፎካካሪ ከርቲስ ሲልዋ ናቸው። አያቱ ይሆናሉ። በዝረራ ነው ያሸነፋቸው።

በከተማዋ በመቶ ዓመት ታሪክ በእሱ ዕድሜ የኒው ዮርክ ከንቲባ የሆነ ሰው የለም።

ለመጨረሻ ጊዜ ለኒው ዮርክ ወጣት ከንቲባ የተመረጠው በአድዋ ጦርነት ዘመን ነው። በ1890ዎቹ አካባቢ።

ዞህራን ማምዳኒ ከወጣትነቱ ባሻገር በብዙ ነገሩ ይለያል። ሙስሊም ነው።

በጥቅሉ አሜሪካዊያን ሙስሊም፣ ጥቁር እና ሴት እንደ መሪ ለመቀበል እምብዛም የተዘጋጁ አይደሉም ተብለው ይታማሉ።

ለዚህም ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ ካማላ ሐሪስን ገፍተው አወዛጋቢውን ዶናልድ ትራምፕን መርጠዋል።

ኒው ዮርካዊያን ግን ይለያሉ። ኒው ዮርክ የእንግሊዝ አፍ 'ሜልቲንግ ፖት' የሚላት ከተማ ናት። ሰው ወደ ከተማዋ ሲገባ ቀልጦ ኒው ዮርካዊ ይሆናል። ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት እያለ ራሱን መሰነጣጠቁን ያቆምና I AM New Yorker [ኒው ዮርካዊ ነኝ] ማለት ይጀምራል።

ማምዳኒም እንዲያ ነው የሆነው።

የተወለደው በአፍሪካዊቷ ኡጋንዳ ውስጥ ነው። የቤተሰቦቹ ዘር ከሕንድ ነው። ኤዲያሚን ዳዳ በሕንዶች ላይ ሲዘምት ወላጆቹ ወደ ከኡጋንዳ እንግሊዝ ሸሹ። ኤዲያሚን ሲሞት ወደ ኡጋንዳ ተመለሱ።

እሱ በሰባት ዓመቱ አሜሪካ ገባ። የኒው ዮርኳ ክዊንስ ክፍለ ከተማ አቅልጣ በድጋሚ ወለደችው። አሁን ማምዳኒ ማን ነው ቢባል "ኒው ዮርካዊ" ብቻ ይሆናል መልሱ።

ያም ሆኖ የዓለም ሕዝቦች ከተማ የሆነችው ኒው ዮርክና ነዋሪዎቿን ድምጽ ስለሰጡት አንድ በአንድ አመስግኗል።

ለመሆኑ ኢትዮጵያዊያንን አመሰገነ? ምን ሲል?

""የመናውያን የመደብር ባለቤቶች፣ ሴኔጋላውያን የታክሲ ሹፌሮች፣ ኡዝቤክስታናውያን ነርሶች እና ኢትዮጵያውያን 'አክስቶች'"

ሲል የመጤዎች ከተማ ለሆነችው ለታላቋ ኒው ዮርክ ከንቲባነት ለመረጡት ኒው ዮርካውያን ምሥጋና ባቀረበበት ጊዜ ኢትዮጵያውያኑን ኒው ዮርከሮች በስም ጠርቶ አመሥግኗል።

ማምዳኒ ምላሱ ይታዘዝለታል። ሂንዱ፣ ኡርዱ፣ ሉጋንዳ፣ አረብኛ እና ስፓኒሽ ቋንቋዎችን ያቀላጥፋል።

አባቱ ከፑንጃብ እናቱ ከሙምባይ ናቸው።

ሚስቱ ከሶሪያ ናት። ከባሌቤቱ ጋር የተገናኙት በፍቅር የትውውቅ መተግበሪያ ዴቲንግ አፕ ነው።

ወላጆቹ የዋዛ አይደሉም። በስኬት መሰላል ጫፍ የነኩ ናቸው።

እናቱ በፊልሙ ዘርፍ ስመ ጥር የሆኑ እና በርካታ ሽልማቶችን የተቀበሉት የፊልም ዳይሬክተር ናቸው፤ ሚራ ናይር ይባላሉ።

አባቱ 'አፍሪካ አፈራቻቸው ከሚባሉ ጎምቱ ፕሮፌሰሮች አንዱ ናቸው። አሁን እዚያው አሜሪካ ውስጥ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ያስተምራሉ።

ሁለቱም ወላጆቹ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በዝነኛው በሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ ነው።

ዞህራን ከወላጆቹ ጋር ወደ ኒው ዮርክ ያቀናው ገና በሰባት ዓመቱ ነው።

የማምዳኒ መጪ ዘመናት ምን ሊሆኑ ይችላሉ ብለን ብንተነብይ በድሉ ላይ ውሃ መቸለስ ይሆን ይሆናል።

ቢሆንም ዶናልድ ትራምፕ የማምዳኒን ሕይወት ሊያከብዱበት ይችላሉ።

ለብዙ ፕሮጀክቶች የሚውል የፌዴራል መንግሥት ድጎማን ሊይዙበት ይችላሉ። ይህን ማድረግ ለትራምፕ ቀላል ነው አይባልም። ማምዳኒ እና ኒው ዮርከሮችም ይህ ሲሆን ዝም ብለው ይመለከታሉ?

አይመለከቱም።

ነገሩ ወደ ፍርድ ቤት መሄዱ የማይቀር ነው።

ትራምፕ ተቃውሞ እየገጠማቸውም በሌሎች የአሜሪካ ከተሞች እንዳደረጉት አሁን ወደ ኒው ዮርክ የአገሪቱን ብሔራዊ ዘብ አሰማራለሁ ብለዋል። ማምዳኒ ደግሞ 'ይሞክሯትና እንተያያለን' እያለ ነው።

ትራምፕ ይህ አበሳጭቷቸዋል። ወታደሮች ወደ ኒው ዮርክ ከተማ እንዳይገቡ ማምዳኒ ካደረገ 'የፊጥኝ አሳስሬ ዘብጥያ እወረውረዋለሁ' ብለዋል።

ይህም ሌላ ውጥረት ፈጥሯል።

የትራምፕ እና የማምዳኒ ጦርነት የተጀመረው ዛሬ አይደለም።

ገና ማምዳኒ እንደሚያሸነፍ ምልክቶች ሲታዩ የቀድሞውን የኒው ዮርክ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስን 'ወደ ሳዑዲ በአምባሳደርነት ልላክህና ማምዳኒን ለሚያሸንፍ ሰው የውድድር ሜዳውን ልቀቅ' ብለውት ነበር።

ይህ ነገር ብዙም አልዘለቀም።

በኋላ ትራምፕ የእሱን ተቀናቃኞች በተለይም ለአንድሩ ኩሞ ድጋፍ ሰጡ። እሱም አልሆነም።

ማምዳኒ በድል ማግስት ባደረገው ንግግር ትራምፕን እንዲህ በነገር ሸንቆጥ አድርጓቸዋል።

"ዶናልድ ትራምፕ ሆይ። እርግጠኛ ነኝ አሁን በቴሌቪዥን እኔን እየተመለከቱ ነው። ለአርስዎ በአራት ቃላት ብርቱ መልዕክት አለኝ. . .

"እባክዎ ድምጹን ከፍ ያደርጉት"

ኒው ዮርከሮች ማምዳኒን ለምን ወደዱት?

አዲስ ነገር ይዞ ስለመጣ።

ዞህራን በኒው ዮርክ ሁሉም የአውቶብስ የትራንስፖርት አገልግሎት ነጻ እንዲሆን፣ የቤት ኪራይ እንዳይጨምር ዕግድ መጣል፣ ተመጣጣኝ ቤትን መገንባት፣ ጤናማ የሸቀጥ ፍጆታዎችን በአነስተኛ ዋጋ ማቅረብ፣ ነጻ የልጆች እንክብካቤ ማቅረብ ፖሊሲዎችን እተገብራለሁ ብሏል።

የኒው ዮርክ የፖሊስ በጀትን ለመቀነስ ዝቷል።

ዞህራን እስራኤልን ከሚቃወሙ ፖለቲከኞች አንዱ ሲሆን፣ በጋዛ እየተፈጸመ ያለውን "የዘር ጭፍጨፋ ነው" በሚል በተደጋጋሚ ሲናገር ያለ ፍርሃት ነው።

ይህ ደግሞ ከኔታንያሁ እና ከአክራሪ ደጋፊዎቻቸው ጋር ያላትመዋል።

ዞህራን ከጥቂት ወራት በፊት ከታዋቂው ጋዜጠኛ መህዲ ሐሰን ጋር በነበረው ቆይታ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ኒው ዮርክ ቢመጡ ምን ታደርጋለህ? ተብሎ ለቀረበለት ችግር እንደሚገጥማቸው ተናግሯል።

ዞህራን ፈርጠም ብሎ "እንደ ከንቲባ ኔታንያሁ ኒው ዮርክ ቢመጣ አሳስረው ነበር" ሲል መልሷል።