ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን እያሰቡ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በአመራራቸው ላይ ከፍተኛ ትችት በሚሰነዘርበት በአሁኑ ወቅት ለሦስተኛ ጊዜ የሥልጣን ዘመን “በንቃት እያሰቡ” እንደሆነ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለተኛ ጊዜ ሙሉ የሥልጣን ዘመናቸው ዘመን እስከ አውሮፓውያኑ 2028 ወይም 2029 ድረስ ማገልገል ይፈልጋሉ ወይ ተብለው ተጠይቀው ነበር።
“በአሁኑ ወቅት ለሦስተኛው የሥልጣን ዘመን እና ከዚያ ምን ሊፈጠር እንደሚችል በንቃት እያሰብኩ ነው፤ ነገር ግን በወቅቱ ስደርስበት እገመግመዋለሁ” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ሆኖም አንድ የፓርላማ አባል ሕጎቹ ተቀይረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን እንዲወርዱ ሌላ የመተማመን ድምፅ (ኮንፊደንስ ቮት) እንዲደረግባቸው ጠይቀዋል።
በኮመንዌልዝ የመሪዎች ስብሰባ ላይ በተገኙበት በሩዋንዳ ፣ ኪጋሊ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየታቸውን እንዲያብራሩ ተጠይቀው “ለሦስተኛ ጊዜ በአውሮፓውያኑ 2030ዎቹ አጋማሽ ላይ እያሰብኩ ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰን ፓርቲያቸውን ወደ ቀጣዩ ምርጫ እንደሚመሩ ገልፀው፣ በመላ አገሪቱ ያለውን መበላለጥ ለማስተካከል እቅዳቸውን ወደፊት መቀጠል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። መንግሥታቸው ይህንን እርምጃ “ደረጃ ማሳደግ” ብሎ ነው የሚጠራው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን እኩልነት ማምጣት ጊዜ እንደሚወስድ ቢያምኑም፣ በሁለቱ ፓርላማዎች በሚደረገው ከፍተኛ ማሻሻያ ሊሳካ እንደሚችልም አክለዋል።
“እኔን እዚህ ቦታ ላይ እርሱኝ። ይህች አገር፣ እንግሊዝ ምን ማድረግ እንደምትችል እና የት እንዳለች አስቡ” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
"መንግሥትን ለመለወጥ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ወስደናል። ለምሳሌም የአገሪቱን ሕገ-መንግሥት እና የሕግ ሥርዓታችንን፣ ድንበሮችን የምናስተዳድርበትን መንገድ፣ ኢኮኖሚያችንን እና የምንሰራቸውን ሁሉንም ዓይነት ሥራዎች በተለየ መንገድ እየሰራን ነው” ብለዋል።
"እንዲሁም በአገር ደረጃ አንድ ታላቅ ፕሮጀክት ጀምረናል። ይህም አንድነት እና ደረጃን ከፍ የሚያደርግ ነው። በዚህ ፕሮጀክት አስደናቂነት በልበ ሙሉነት አምናለሁ” ብለዋል ።












