የድንበር አጥር ጥሰው ወደ ስፔን ለመግባት የሞከሩ በርካታ ስደተኞች ሕይወታቸው አለፈ

የተጎዳን ስደተኛ ደግፈው የሚሄዱ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, APA

የምስሉ መግለጫ, የስፔን ባለሥልጣናት እንዳሉት ከ100 በላይ የሚሆኑት ስደተኞች ወደ ክልሉ መግባት ችለዋል።
ታትሟል

ስፔንን ከሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ በሚለየው ሜሊላ ግዛት ድንበር ተሻግረው ወደ ስፔን ለመግባት የሞከሩ በርካታ ስደተኞች ሕይወታቸው ማለፉ ተገለጸ።

 የሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ ባለሥልጣናት እንዳሉት፣ አርብ ዕለት ስደተኞቹ አገሪቷን ከስፔን በሚለየው ግዛት፣ ሜሊላ አቋርጠው ወደ ስፔን ለመግባት ሲሞክሩ ቢያንስ 23 ስደተኞች ሲሞቱ፤ ሌሎች ደግሞ ለጉዳት ተዳርገዋል።

የተወሰኑት ስደተኞች ሕይወታቸው ያለፈው ድንበር ላይ ከተገነባው ረዥም አጥር ላይ ወድቀው መሆኑንም ዘገባዎች አመልክተዋል።

አርብ ዕለት ድንበር ላይ በስደተኞችና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረው ግጭትም የተጎዱ ስደተኞችና የጸጥታ አካላት ሆስፒታል መግባታቸው ተገልጿል።

ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ስፔንና ሞሮኮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እንደገና ከጀመሩ በኋላ በርካታ ስደተኞች ድንበሩን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት ተቀዛቅዞ የነበረው ስፔን አወዛጋቢ ለሆነው የሞሮኮ ምዕራብ ሳህር ክልል ድጋፍ ካደረገች በኋላ ነው።

የስፔን ባለሥልጣናት እንዳሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ በርካታ ስደተኞች የድንበር አጥሩን በመቁረጥ ወደ ክልሉ ለመግባት ሞክረዋል።

አብዛኞቹ እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን ከ100 የሚበልጡት ግን ማለፍ ችለው በስደተኞች መቀበያ ጣቢያ እየተስተናገዱ መሆኑንም ባለሥልጣናቱ አክለዋል።

በአደጋው መጀመሪያ ላይ የ18 ስደተኞች ሕይወት ያለፈ ሲሆን ቅዳሜ ዕለት አምስት ተጨማሪ ስደተኞች በደረሰባቸው ጉዳት ሳቢያ ሕይወታቸው ማለፉን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

ሜሊላ እና ሴውታ የስፔን ግዛቶች ሲሆኑ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት የሚሄዱ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚሞክሩባቸው ዋነኛ መንገዶች ሆነዋል።