የታደጓቸው የሰሜን ኮሪያ ታዳጊዎች ላይ ጥቃት ያደረሱት ፓስተር ለእስር ተዳረጉ

ታትሟል

በመቶዎች የሚቆጠሩ ከሰሜን ኮሪያ አገዛዝ አምልጠው የሸሹ ታዳጊዎችን በመታደግ ጀግና ተብለው የነበሩት የደቡብ ኮሪያው ፓስተር በታደጓቸው ለአካለ መጠን ባልደረሱ ታዳጊዎች ላይ ወሲባዊ ጥቃቶች ፈጽመዋል በሚል ለእስር ተዳረጉ።

የ67 ዓመቱ ቹን ኪዎን በሴኡል በሚገኘው ለታዳጊዎቹ በከፈቱት የአዳሪ ትምህርት ቤታቸው ውስጥ ባደረሱት ወሲባዊ ጥቃት የአምስት ዓመት እስር ተፈርዷባቸዋል።

ፓስተሩ ለበርካታ አስርት ዓመታት እንደ አዳኝ ይቆጠሩ የነበሩ ሲሆን ከሰሜን ኮሪያ አገዛዝ ለሚያመልጡት በርካቶችንም መንገድ በማመቻቸት ይሞገሱም ነበር።

ፓስተሩ ለእስር የተዳረጉት መስከረም ወር ላይ በደቡብ ኮሪያ መዲና ሴኡል ነበር።

ፖሊስ እንደሚለው ፓስተሩ ከሰሜን ኮሪያ አገዛዝ ሸሽተው የመጡ ስድስት የሰሜን ኮሪያ ታዳጊዎች ላይ ዱሪሃና በተሰኘው የአዳሪ ትምህርት ቤታቸው ላይ ወሲባዊ ጥቃት አድርሰዋል።

ቹን ክሱን ውቅድ ቢያደርጉም ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ረቡዕ በዋለው ችሎት ተጎጂዎች ያቀረቡት ማስረጃ ፍጹም አስተማማኝ ነው ሲል ውሳኔውን አስተላልፏል።

“ተጎጂዎቹ በተደጋጋሚ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። እናም ከሰጧቸው ምስክርነቶች መካከል ካልደረሰባቸው ሰዎች ውጭ ሊገለጹ የማይችሉ ይዘቶችን ያካትታል” ሲሉም የሴኡል መካከለኛ አውራጅ ፍርድ ቤት ዳኛ ሴኡንግ ጂኦንግ ኪም ተናግረዋል።

በስድስት ለአካለ መጠን ባልደረሱ ታዳጊዎች ላይ የወሲብ ጥሰት አድርሰዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው ግለሰብ ፍርድ ቤቱ በአምስቱ ጥፋተኛ ሆኖ አግኘቻቸዋሉ የሚል ብያኔ አስተላልፏል።

ታዳጊዎቹ አንዳንዶቹ ብቻቸውን ከሰሜን ኮሪያ የሸሹ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በቹን ተልዕኮ አጋዥነት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው ከሰሜን ኮሪያ ያመለጡ ናቸው ተብሏል።

ቹን በደቡብ ኮሪያ ውስጥ ስመ ጥር ከሆኑት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነውን ዱሪሃናን የመሰረቱ ሲሆን ይህም ድርጅት ከሰሜን ኮሪያ አገዛዝ ማምለጥ የሚፈልጉ ሰዎችን በቻይና በኩል እንዲያመልጡ መንገድ የሚያመቻች ነው።

ላለፉት 25 ዓመታትም ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰሜን ኮሪያውያንን ጨቋኝ ከሆነው የኪም ቤተሰቦች አገዛዝ እንዲያመልጡ መርዳቱን ፓስተሩ ተናግረዋል። ከዚህም ስራቸው ጋር ተያይዞ የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ፓስተሩ ላይ ውግዘት አድርሶባቸዋ።

በአውሮፓውያኑ 2002 በቻይና በማስመለጥ ተልዕኮ እያሉም ለሰባት ወራት እስር መዳረጋቸውንም ተከትሎ የበርካታ ሚዲያዎችን ቀልብ ስቦ ነበር።

ከሰሜን ኮሪያ ላመለጡ ታዳጊዎች አማራጭ ትምህርት ቤት መመስረትን ጨምሮ ስራዎቻው በሰፊው ተዘግቧል። ከነዚህም መካከል ዘጋቢ ፊልሞች እንዲሁም ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ ኒውዮርክ ታይምስ እና ናሽናል ጂኦግራፊን ጨምሮ ሌሎች ሚዲያዎች ሰፋ ያሉ ጽሁፎች አቅርበዋል።

ግለሰቡ በቁጥጥር ስር መዋላቸው እንዲሁም ጥፋተኛ መባላቸው ደቡብ ኮሪያን ያስደነገጠ ሲሆን የፍርድ ሂደቱም በዚህ ሳምንት በተለያዩ ሚዲያዎች ሲዘገብ ቆይቷል።