ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባልተጠበቀ ሁኔታ የወዳጅነት መንፈስ የታየበት የትራምፕ እና የዞህራን ማምዳኒ የመጀመሪያ ውይይት
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ተመራጩ የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ዞህራን ማምዳኒ በዋይት ሐውስ ሲገናኙ ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር የነበረው ዓይነት ንትርክ ውስጥ ይገባሉ የሚለው የብዙዎች ግምት ነበር።
ትናንት አርብ ፕሬዝዳንቱ እና ከንቲባው ሲገናኙ ከተጠበቀው በተቃራኒ ዋይት ሐውስን የሙገሳ ድግስ አድርገውታል።
ዴሞክራቲክ ሶሻሊስት እንደሆነ የሚናገረው ማምዳኒ ምርጫውን ካሸነፈ በኋላ ባደረገው ንግግር ትራምፕ "ጨቋኝ ገዢ" ሲል ጠርቷቸዋል።
አርብ ዕለት ከመገናኘታቸው አስቀድሞ ደግሞ የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ የማምዳኒን ጉብኝት የገለጸችው "ወደ ዋይት ሐውስ የሚመጣው ኮሚኒስት" በሚል ነበር።
ፕሬዝዳንቱ እና ከንቲባው በነጩ ቤተ መንግሥት ኦቫል ኦፊስ ጎን ለጎን ሲቆሙ ግን ያልተጠበቀ የወዳጅነት ድምፀት ተላብሰው ታይተዋል።
ሁለቱም፤ በኒው ዮርክ ያለውን የኑሮ ውድነት ቀውስ ለመፍታት ያላቸው ፍላጎት ደጋግመው ሲገልጹ አምሽተዋል። በርካታ ጊዜያት ፈገግ እየተለዋወጡ ተመልካችን አስገርመዋል።
ትራምፕ፤ ከማምዳኒ ስለተሰነዘሩባቸው ፖለቲካዊ ትንኮሳዎች ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው ጥያቄ ጭምር የመለሱት በተዝናና አኳኋን ነው።
ይህ ሁኔታ ለፖለቲካ ተመልካቾች ያልተገመተ ነበር። ሁኔታው፤ ምናልባትም የፖለቲካ ስኬታቸው የሚመሠረተው የኑሮ ውድነት ቀውሱን በመፍታት እንደሆነ መገንዘባቸውን እንደሚጠቁም ተገምቷል።
ይህ የወዳጅነት መንፈስ በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ማምዳኒ የከንቲባነት ሥልጣኑን ሲረከብም ይቀጥል እንደሆነ የሚታይ ይሆናል። እስከዛው ግን፤ ትራምፕ "እደግፈዋለሁ" ሲሉ መናገራቸውን እንያዝ።
የትራምፕ ሙገሳ
ትራምፕ እና ማምዳኒ በግል ያደረጉትን ውይይት አጠናቅቀው ጋዜጠኞች ፊት ከቆሙበት ጊዜ አንስቶ ድባቡ ያስታውቅ ነበር።
ከጋዜጠኞች ጋር በተገናኙበት ወቅት፤ ማምዳኒ ከጠረጴዛ ላይ ከተቀመጡት ትራምፕ በስተቀኝ እጆቹን አቆላልፎ ቆሞ ታይቷል። የሰውነት እንቅስቃሴ ዘና ማለታቸውን ያሳብቅ ነበር፤ በተለይ የትራምፕ።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ሲያደርጉ እንደቆዩት ማምዳኒን ከመሸንቆጥ ከመቆጠብ አልፈው በርካታ ጊዜያት ሲያደንቁት ታይተዋል። ማምዳኒ "እጅግ ትልቅ ከንቲባ" ይሆናል የሚል ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ቆየት ብለው ደግሞ "በጣም ጥሩ ስራ ማከናወን የሚያስችለውን በራስ መተማመን" የተላበሰ እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
የተድበሰበሱት የጂሃድ እና የፋሺስት ጥያቄዎች
የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ምርጫ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ትራምፕ እና ማምዳኒ ፖለቲካዊ ትንኮሳዎችን ሲሰነዛዘሩ ከርመዋል።
ትናንት በዋይት ሐውስ አንዲት ጋዜጠኛ ትራምፕ ከንቲባውን "ኮሚኒስት" ብለው መጥራታቸውን፤ ማምዳኒ ደግሞ ፕሬዝዳንቱን "ጨቋኝ ገዢ" ማለቱን አስታውሳቸው ነበር። ሁለቱም ከዚህ ቀደም ስለተናገሯቸው ነገሮች በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበው፤ አንዳቸው ሌላኛውን ወደ ማሞገስ ተመልሰዋል።
ማምዳኒ፤ ትራምፕን "ፋሺስት" ብሎ ስለመጥራቱ በተጠየቀበት ጊዜ ጭምር ትራምፕ ጥያቄውን እንዲመልስ አበረታተውታል። "ምንም አይደል፤ አዎ ማለት ትችላለህ። ከማብራራት ይሄ [አዎ ማለት] ይቀላል" ሲሉ ፖለቲካዊ ምላሽ መስጠት ጀምሮ የነበረውን ማምዳኒን ደግፈዋል።
ትራምፕ ስለ ማምዳኒ ከሰጡት አስተያየት ለትችት የቀረበው "ትንሽ ወጣ ያሉ አመለካከቶች አሉት" በማለት የተናገሩት ነው።
ፕሬዝዳንቱ፤ ለኒው ዮርክ ግዛት ገዢነት እየተወዳደሩ ያሉት ሪፐብሊካኗ ኤልሲ ስቴፋንኪ ማምዳኒ ላይ ስላሰሙት ፍረጃ የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ ሲያደርጉም ታይተዋል።
"አሁን ኦቫል ኦፊስ ውስጥ ከ 'ጂሃዲስት' ጎን እንደቆሙ ያስባሉ?" በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ "እንደዚያ አላስብም" ሲሉ በፍጥነት መልሰዋል።
"አንዳንዴ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ስትሆን ነገሮችን ትናገራለህ" ሲሉ በሪፐብሊካኗ የኮንግረስ አባል የተሰነዘረውን ፍረጃ አድበስብሰዋል።
የኑሮ ውድነት ጉዳይ
ምናልባትም ማምዳኒ እና ትራምፕ በዚህ መልኩ የተግባቡ መስለው እንዲታዩ ያደረጋቸው የኑሮ ውድነት ጉዳይ ላይ ያላቸው የጋራ አቋም ነው።
ትራምፕ ወደ ሥልጣን የመለሳቸውን ምርጫ ያሸነፉት የአሜሪካ ዜጎችን ያማረረውን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ደጋግመው ካነሱ በኋላ ነበር። የአስቤዛ እና ሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች ወጪ በየጊዜው መጨመሩን የሚያነሱት ትራምፕ፤ የኢኮኖሚ መረጋጋትን ማምጣት አንዱ መልዕክታቸው እንዲሆን አድርገዋል።
ማምዳኒን በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ተመጣጣኝ ዋጋ የሚከፈልበት መኖሪያ ቤት እጥረት መኖሩን በማንሳት የኪራይ ዋጋ ጭማሪን ባለበት ለማቆየት ቃል ገብቷል።
በትናንቱ ስብሰባቸው እንዴት "ተመጣጣኝ ዋጋን ለኒው ዮርክ ነዋሪዎች ማድረስ" እንደሚቻል መነጋገራቸውን ማምዳኒ ገልጿል።
ከትራምፕ ጋር ስለሚያቃርኑት ምልከታዎቹ ጥያቄ በተነሳለት ቁጥር ንግግሩን ወደ እነዚህ ነጥቦች ሲመልስ ታይቷል።
የተለያየ አቋም ከያዙባቸው ነጥቦች አንዱ ስለሆነው በመካከኛው ምሥራቅ ሰላም የማምጣት ጉዳይ ለማምዳኒ ጥያቄ ተነስቷል። ተመራጩ ከንቲባ ምላሽ የሰጠው፤ የትራምፕ ደጋፊዎች "የዘላለም ጦርነቶች እንዲቋጩ" እንዲሁም መሪዎች "የኑሮ ውድነት ቀውስን" እንዲፈቱ ያላቸውን ምኞች እንደገለጹለት በመናገር ነው።
ሕግ ማስከበር እና ስደተኞችን በተመለከተም የሚያግባባቸው ነጥብ ያገኙ መስለው ታይተዋል። የፌደራል መንግሥት በኒው ዮርክ ስለሚያከናውነው ከስደተኞች ጋር የተያያዘ ሕግ የማስከበር ተግባር በተመለከተ መነጋገራቸውን ማምዳኒ ገልጿል።
ሕግ ማስከበሩ የሚከናወንበትን መንገድ በተመለከተ ከነዋሪዎች የተነሳውን ስጋት ለፕሬዝዳንቱ ማስረዳቱንም አክሏል።
ትራምፕ ግን ከስደተኞች ይልቅ በከተማዋ ስለሚታየው የወንጀል ምጣኔ ጉዳይ መነጋገራቸውን ገልጸዋል። ፕሬዝዳንቱ፤ "[ኒው ዮርክ ውስጥ] ወንጀል መመልከት አይፈልግም፤ እኔም ወንጀል መመልከት አልፈልግም" ሲሉ በዚህ ጉዳይ መስማማታቸውን ጠቁመዋል።
ትራምፕ ከማምዳኒ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት እንደሚስማሙ "ጥርጣሬ እንደሌላቸው" ተናግረዋል። አክለውም፤ ማምዳኒ በሚመራት ኒው ዮርክ ውስጥ ቢኖሩ ደህንነት እንደሚሰማቸው ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።