ለግብጽና እስራኤል ስንዴ ለመጫን ሁለት መርከቦች ዩክሬን ደረሱ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሁለት የጭነት መርከቦች በጥቁር ባሕር አቋርጠው የዩክሬን ወደብ መድረሳቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ።
ሁለቱ መርከቦች ለዓለም ገበያ የሚቀርብ 20 ሺህ ቶን ስንዴ ለመጫን፣ ቾርኖሞርስክ ወደብ ቅዳሜ ዕለት መድረሳቸው ተሰምቷል።
ባለሥልጣናቱ ሩስያ ለእህል ጫኝ መርከቦቹ ዋስትና ለመስጠት የገባችውን ስምምነት ካፈረሰች በኋላ የሲቪል መርከቦች ወደ ዩክሬን ወደብ ሲደርሱ የመጀመርያው ነው ተብሏል።
ከዚህ በፊት ይህ መተላለፍያ ሆኖ ያገለግል የነበረው ከዩክሬን ለሚነሱ መርከቦች ብቻ ነበር።
የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ኦሌክሳንደር ኩብራኮቭ፣ እንዳሉት መርከቦቹ የዩክሬን፣ ቱርክ፣ አዘርባጃን እና ግብጽ ዜጎችን የያዙ ሲሆን የሚያውለበልቡትም የፓላኡ ኦሽኒክ አይላንድ ባንዲራን ነው።
ሪዚሊያንት አፍሪካ እና አሮያት የተሰኙት የጭነት መርከቦች ለግብጽ እና እስራኤል የሚላኩ ስንዴ እንደሚጭኑ የዩክሬን ግብርና ሚኒስቴር ተናግሯል።
ሩስያ በዩኤን ከሚደገፈው እና ስንዴ ከዩክሬን ወደቦች መላክ የሚያስችለውን ስምምነት ጥላ ከወጣች በኋላ ኪየቭ በተናጠል የባሕር ኮሪደሩን ፈቅዳለች።
ሞስኮ የስምምነቱ አካል የሆነው እና የአገሪቱን ምግቦች እና ማዳበርያዎች ለውጪ ገበያ ማቅረብ የሚለው ስምምነት አልተከበረልኝም፣ ምዕራባውያን የጣሉብኝ ማዕቀብ የግብርና ምርቶቼን ለውጪ ገበያ እንዳላቀርብ ጫና አሳድረውብኛል ስትል ቅሬታ ታቀርባለች።
ከዚያ በኋላም ወደ ዩክሬን የሚቀዝፉ የሲቪል መርከቦችን እንደ ወታደራዊ ዒላማ እንደምታያቸው በመግለጽ አስጠንቅቃ ነበር።
በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ሩስያ በዩክሬን የባሕር ወደብ የቆመ መርከብን በተምዘግዛጊ ሚሳዔል ለመምታት ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጋለች ሲል ወንጅሏል።
ዩክሬን ለዓለም ገበያ እንደ የሱፍ ዘይት፣ ገብስ፣ በቆሎ እና ስንዴ ያሉ ምርቶች ከፍተኛዋ አቅራቢ ናት።
ሩስያ ዩክሬንንን እኤአ በየካቲት ወር 2022 በወረረችበት ወቅት፣ የአገሪቱን የጥቁር ባሕር ወደቦች አግዳ ለውጭ ገበያ ዝግጁ የነበረ 20 ሚሊዮን ቶን እህልን እንዳይንቀሳቀስ አድርጋ ነበር።
ይህም የዓለም ከዩክሬን እህል የሚያስገቡ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ላይ እጥረት የፈጠረ ሲሆን፣ የምግብ እህል ዋጋም ከፍተኛ ጭማሪ እንዲያሳይ አድርጓል።
አፍጋኒስታን፣ የመን፣ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው አገራት መካከል ናቸው።
በጥቁር ባሕር የሚያልፉ መርከቦች ላይ ከመዛት ባለፈ ሞስኮ የዩክሬን ወደቦች መሠረተ ልማትን ዒላማ አድርጋለች።
በተደጋጋሚም ለዓለም ገበያ የሚጫኑ እህሎች የሚጫኑባቸው ወደቦችን፣ ኢዝሜይል እና ሬኒን ያጠቃች ሲሆን በዚህም የተነሳ ዓለም ላይ የምግብ እጥረት እንዲፈጠር ሆን ብላ ትሠራለች ስትል ዩክሬን ትከስሳለች።












