ጠቅላይ ሚኒስተር ቦሪስ ጆንሰን ከፓርቲያቸው መሪነት ለቀቁ፣ ከወራት በኋላም ሥልጣን ይለቃሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስተር ቦሪስ ጆንሰን ከካቢኔ ሚኒስትሮቻቸውና ከምክር ቤት አባላት ድጋፍ ሳያገኙ በመቅረታቸው ከወግ አጥባቂው ፓርቲያቸው መሪነት ሊለቁ ነው።
በዚህም ለፓርቲው መሪነት የሚደረገው ፉክክር በቅርቡ የሚደረግ ሲሆን፣ በቀጣይ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ደግሞ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስተር ይሰየማል።
አስከዚያው ድረስ ግን ቦሪስ ጆንሰን በአገሪቱ የጠቅላይ ሚኒስትር መንበር ላይ ይቀጥላሉ።
ጆንሰን በአመራራቸው ላይ በርካታ ትችቶች ሲቀርብባቸው ቆይቶ በርካታ ባለሥልጣኖቻቸው በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ ነው ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት።
ከእነዚህም መካከል ቻንስለር ናዲም ዛሃዊን ጨምሮ ከፍተኛ ካቢኔ አባሎቻቸው “በክብር የሥልጣን መንበራቸውን እንዲለቁ” ለጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጥያቄ አቅርበው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ሪሺ ሱናክን ጨምሮ በርካታ ሚኒስትሮቻቸው አመራራቸውን በመቃወም በ48 ሰዓታት ውስጥ በፈቃዳቸው ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ ነው።
በተመሳሳይ ቦሪስ ጆንሰን ሥልጣን እንዲለቁ የቀረበላቸውን ጥያቄ እስከ ሐሙስ ረፋድ ድረስ ሳይቀበሉት ቆይተው፣ የፓርላማ አባሎቻቸውን ድጋፍ ማግኘት ሳይችሉ በመቅረታቸው በመጨረሻ ወስነዋል።
ሚኒስትሮቻቸው በፈቃዳቸው ሥልጣን በመልቀቃቸውና የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ከፓርላማ አባላት ማግኘት ያልቻሉት ቦሪስ ጆንሰን ከፓርቲው መሪነት ስለመልቀቃቸው መግለጫ እሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም ከወራት በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ያስረክባሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በፓርቲያቸው ውስጥ የተደረገውን ውድድር በማሸነፍ በ2019 ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት። ከአምስት ዓመት በኋላ በከፍተኛ የድምጽ ብልጫም ምርጫ አሸንፈዋል።
ምርጫውን ሲያሸንፉ የብሬግዚት (ዩናይትድ ኪንግደም ከአውሮፓ ኅብረት የመውጣት) ሂደትን እቋጫለሁ ብለው ቃል ገብተው አሳክተዋል።
ቢሆንም ግን መንግሥታቸው ባለፉት ወራት በብዙ አወዛጋቢ ጉዳዮች ውስጥ ቆይቷል። በኮሮናቫይረስ የእንቅስቃሴ ገደብ ወቅት በጽህፈት ቤታቸው ውስጥ በርካታ ሰዎች የታደሙበት ድግስ ማካሄዳቸው እና በፖሊስ መመርመሩም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
በበዚህ ሳምንት ደግሞ የቀድሞው ምክትል የፓርቲያቸው ተጠሪ ክሪስ ፒንቸር ላይ የቀረበውን ተገቢያ ያልሆነ ፆታዊ ድርጊትን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያያዙበት መንገድ ነውጥ ቀስቅሶባቸዋል።
















