ፑቲን አውሮፓ እራሷን ከጥቃት መከላከል የምትችልበት ደረጃ ላይ አይደለችም ሲሉ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድርሚር ፑቲን አውሮፓውያን አገራት የጦርነት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት ባለመገንባታቸው ለጥቃት የተጋለጡ ናቸው ሲሉ ተናግሩ።
ፕሬዝዳንቱ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ባላት ጦርነት ኪዬቭን የሚደግፉ አውሮፓውያን አገራትንም አስጠንቅቀዋል።
“የአሜሪካውያኑ እንኳ ወደ አውሮፓ መጥቶ ቢደመር ሩሲያ በአውሮፓ ምድር ካለ (የኒውክሌር ጦር መሳሪያ) በላይ አላት” ሲሉ ተናግረዋል።
ፑቲን ይህን አስተያየት የሰጡት በሴንተር ፒተርስበርግ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሃብት ፎረም ላይ ነው።
በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ሞስኮ አስፈላጊ ሆና ካገኘችው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ልትጠቀም እንደምትችል ሲናገሩ የቆዩት ፑቲን፤ ትናንት ቅዳሜ ሰኔ 1/2016 ዓ.ም. ሲናገሩ ግን ሩሲያ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማሸነፍ ኒውክሌር መጠቀም አይጠበቅባትም ብለዋል።
ፑቲን አገራቸው ሩሲያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋል የሚችለው መቼ ነው የሚለውን መርህ ግን መቀየር የለባትም ብዬ አላስብም ብለዋል።
“በመላው ዓለም እየተከናወነ ያለውን ነገር በቅርበት እየተከታተልን ነው” ያሉት ፑቲን፤ አገራቸው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሙክራን ጨምሮ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ መጠቀም ይኖርባታል የሚለውን መመሪያ ልትከልስ ትችላለች ብለዋል።
ፑቲን ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ ስለማዋል የሚናገሩት ታክቲካል ኒውክሌር ጦር መሳሪያ ከኒውክሌር ቦምብ በተለየ በዒላማው ዙሪያ ላይ ብቻ ውድመት የሚያስከትል ነው።
በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ የተካሄደው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም ምንም እንኳ ሩሲያ ጦርነት ውስጥ ብትገኝም የዩክሬን ጦርነት ከዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት እንዲሁም ኢኮኖሚያዋ ላይ ጉልህ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳላመጣ ማሳያ ነው የሚሉ አልጠፉም።
በሌላ በኩል ፑቲን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ያሰቡት ወታደራዊ ዘመቻ ሦስት ዓመት ለመድፈን እየተቃረበ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በምዕራባውያን በርካታ ማዕቀብ የተጣለበት አገር ሩሲያ ሆናለች።
ከዚህ በተጨማሪ በሩሲያ እና በምዕራባውያን መካከል ያለው ውጥረት ከሰሞኑ አይሏል። በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ፑቲን ምዕራባውያንን ለማጥቃት የሚውል የረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ጦር መሳሪያዎችን የተለያዩ አገራትን ልታስታጥቅ ትችላለች ማለታቸው ይታወሳል።
ፑቲን ይህን ያሉት በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጦር መሳሪያ ዩክሬን በሩሲያ የሚገኙ ዒላማዎችን እንድታጠቃ የድርጅቱ አባላት መፍቀዳቸውን ተከትሎ ነው።
በትናንትናው ቃለ መጠይቅ ላይም ፑቲን ይህንን ሃሳባቸውን በማጠናከር ተናግረዋል።
“እስካሁን ድረስ እነዚህን መሳሪያዎች አላቀረብንም ይሁን እንጂ ለዩክሬን ጦር መሳሪያ በማቅረብ የሩሲያ አካባቢ እንዲመቱ በሚፈቅዱ አገራት ጫና ስር ለገቡ አገራት ወይም ሕጋዊ እውቅና ላላቸው ቡድኖች የማስታጠቅ መብት አለን” ብለዋል።
ፑቲን የትኞቹን አገራት ወይም ቡድኖች ረዥም ርቀት ተመዘግዛጊ መሳሪዎችን እንደሚያስታጥቁ በስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።












