ምባፔን በውሰት ወደ ሊቨርፑል ይመጣል? አሜሪካዊው ራፐር ጄይ ዚ ቶተንሃም ይገዛ ይሆን?

ታትሟል

ሊቨርፑል፤ ምባፔን በውሰት ለማምጣት ከፈረንሳዩ ክለብ ፓሪ ሳን ዠርማ ጋር ድርድር መጀመራቸውን ሰንደይ ሚረር ዘግቧል።

የሳዑዲ አረቢያው ክለብ አል ሂላል በ259 ሚሊዮን ፓውንድ የ24 ዓመቱ ፈረንሳዊ አጥቂ ለመግዛት ጥያቄ አቅርቦ ተጫዋቹ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

በሌላ በኩል የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ ምባፔን በቋሚነት ለመግዛት 198 ሚሊዮን ፓውንድ መመደቡን ማርካ አስነብቧል።

ሊቨርፑል ቤልጂየማዊውን የ19 ዓመት አማካይ ሮሜዮ ላቪያ ከሳውዝሃምፕተን ለማምጣት እየሞከሩ ነው ሲል ሊቨርፑል ኤኮ አስነብቧል።

ቀያዮቹ ከዚህ ቀደም ተጫዋቹን በ34 ሚሊዮን ፓውንድ ለመግዛት ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ሆኗል።

አሜሪካዊው ጉምቱ የሙዚቃ ሰው ጄይ ዚ ቶተንሃም ሊገዛው እንደሚችል ሰንደይ ኤክስፕረስ ፅፏል።

እንደዘገባው ከሆነ የቶተንሃም ባለቤት የሆኑት ጆ ሌዊስ በተጠረጠሩበት የማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ጄይ ዚ ክለቡን ለመግዛት ጥያቄ ያቀርባል።

አስተን ቪላ የ27 ዓመቱን ስፔናዊ የክንፍ መስመር ተጫዋች አዳማ ትራኦሬ ለማስፈረም እየጣሩ ነው። ትራኦሬ ከዎልቭስ ከተሰናበተ በኋላ እስካሁን ክለብ አላገኘም።

ባየርን ሙኒክ የቶተንሃሙን አጥቂ ሃሪ ኬን የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት እንደሚያስፈርሙት እርግጠኛ ናቸው ሲል ስካይ ስፖርትስ ዘግቧል።

ሰኞ ዕለት የቶተንሃሙ ሊቀ መንበር ዳንኤል ሌቪ እና የባየርን ሙኒክ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስብሰባ እንደሚቀመጡና ሙኒክ ሃሪ ኬንን ለመግዛት 75 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚያቀርብ የሜል ሰንድ ዘገባ ያስረዳል።

ስኮት ማክቶሚናይን ለዌስት ሃም ሊሸጡ አቅደው የነበሩት የማንቸስተር ዩናይትዱ አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ የ18 ዓመቱ እንግሊዛዊ ኮቢ ማይኑ መጎዳቱን ተከትሎ ሐሳባቸውን ሊቀይሩ እንደሚችሉ ቴሌግራፍ ፅፏል።

ሴኔጋላዊው አጥቂ ሳዲዮ ማኔ ከባየርን ሙኒክ ወደ ሳዑዲው አል-ናስር ሲያቀና ሊቨርፑል ማግኘት የሚጠብቅባቸውን 7.5 ሚሊዮን ሊያመልጣቸው እንደሆነ የሜል ዘገባ ጠቅሷል።

ማንቸስተር ኢቭንኒንግ ኒውስ እንደፃፈው ማንቸስተር ሲቲ ክሮኤሻዊውን ተከላካይ ጃስኮ ግቫርዲዮል ካስፈረሙ ስፔናዊውን ተከላካይ አይሜሪክ ላፖርት ይሸጡታል።

የሳዑዲ አረቢያው አል-ናስር ብራዚላዊውን የ29 ዓመት ተከላካይ ማርኪኒዮስ ለማስፈረም ቢፈልጉም ፓሪ ሳን ዠርማ ተጫዋቹን ለመሸጥ ዝግጁ አይደለም።

ሮማ ጣሊያናዊውን የዌስት ሃም አጥቂ ጂያንሉካ ስካማካ በውሰት አምጥቶ በ19 ሚሊዮን ፓውንድ ሊገዛው እንደሚችል የጣሊያኑ ካልቺዮመርካቶ አስነብቧል።

አስተን ቪላ የባርሴሎናውን የ23 ዓመት ተጫዋች ፌራን ቶሬዝ ለማስፈረም ቢፈልጉም ያቀረቡት ገንዘብ የተጫዋቹን ፍላጎት የማይመጥን እንደሆነ የስፔኑ ስፖርት ጋዜጣ ፅፏል።