ሪፐብሊካኖች ምክር ቤቱን በጠባብ ውጤት አሸንፈው በድጋሚ ተቆጣጠሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ እንደገመተው ከሆነ በአሜሪካ የአማካይ ሥልጣን ዘመን (ሚድ ተርም) ምርጫ የታችኛውን የኮንግረስ ምክር ቤት አብላጫ ድምጽ ለመያዝ የሚያስፈልጋቸውን 218 ወንበሮች ሪፐብሊካኖች አሳክተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለው የፓርቲው ልዩነት አነስተኛ ቢሆንም፣ የፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን አጀንዳ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ለማቆም በቂ ነው ተብሏል።
አዲሱ ኮንግረስ በጥር ወር ሲሰበሰብ ዲሞክራቶች ሴኔቱን ይቆጣጠራሉ።
በሴኔቱ ጥቂት መቀመጫዎች ገና አለየላቸውም።
ሴኔቱን እና ኮንግረሱን ለመቆጣጠር ተስፋ አድርገው የነበሩት ሪፐብሊካኖች በባለፈው ሳምንት ምርጫ የሚጠብቁትን ያህል አላሳኩም።
የካሊፎርኒያ 27ኛ አውራጃ ወንበር በድጋሚ ማይክ ጋርሲያ ማሸነፋቸው ረቡዕ ዕለት በመታወቁ በምክር ቤቱ የሚፈልጉትን የአብላጫ ወንበር አሸንፈዋል።
የሪፐብሊካኑ ፓርቲ 435 መቀመጫዎች ካሉት ምክር ቤት ከ218 እስከ 223 መቀመጫዎችን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ሲቢኤስ ዘግቧል።
ሰኞ ሪፐብሊካኖች የዲሞክራቷን ናንሲ ፔሎሲ በመተካት በቀጣይ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ እንዲሆኑ ያጯቸው ኬቨን ማካርቲ የምክር ቤቱን የበላይነት በመቆጣጠራቸው ደስታቸውን ገልጸዋል።
የካሊፎርኒያ ኮንግረስ አባል ረቡዕ ምሽት "አሜሪካውያን ለአዲስ ጉዞ ዝግጁ ናቸው። ሪፐብሊካኖች ቃል የገቡትን ለመተግበር ዝግጁ ናቸው" ሲሉ ትዊተራቸው ላይ አስፍረዋል።
አፈ ጉባኤ ሆነው ለመመረጥ የምክር ቤቱ የሪፐብሊካን ፓርቲ አናሳ (ማይኖሪቲ) መሪ ከ435 ምክር ቤት አባላት ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘት አለባቸው።
ፔሎሲ ረቡዕ ምሽት በሰጡት መግለጫ ፓርቲያቸው “በሪፐብሊካን አብላጫ ድምጽ ላይ ጠንካራ ሥራ እንደሚያከናውን” በመግለጽ መዶሻውን በቀላሉ እንደማይተዉ ጠቁመዋል።
የ82 ዓመት የሆናቸው ፔሎሲ መጀመሪያዋ ሴት አፈ ጉባኤ ናቸው።
ፕሬዝዳንት ባይደን ማካርቲን እንኳን ደስ ያለዎት ካሉ በኋላ ከሪፐብሊካኖች ጋር ለአሜሪካውያን ስኬት በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
"ባለፈው ሳምንት እንዳልኩት መጪው ጊዜ በፖለቲካ ጦርነት ውስጥ ከመታሰር ይልቅ በጣም ተስፋ ሰጭ ይሆናል" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
"የአሜሪካ ሕዝብ እንድንሠራላቸው ይፈልጋሉ። በሚፈልጓቸው ጉዳዮች ላይ እንድናተኩር እና ሕይወታቸውን የተሻለ እንድናደርግ ይፈልጋሉ" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የማካርቲ ፓርቲ የፕሬዚዳንቱ ተወዳጅነት ዝቅተኛ መሆን፣ የዋጋ ግሽበት እና የኮንግረሱ ካርታዎች በሪፐብሊካን በሚመሩ የክልል ሕግ አውጪዎች መቀረጻቸው በምርጫው እንደሚያሸንፉ ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር።
ባለፈው ሳምንት የተፈለገው ድል ባለመገኘቱ በዋናነት በሁለት የፓርቲ መሪዎች ተጠያቂ ሆነዋል- የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሴኔቱ መሪ ሚች ማኮኔል።
ማክሰኞ ምሽት የቀድሞው ፕሬዚዳንት በ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሚሳተፉ በይፋ አስታውቀዋል።
ረቡዕ ዕለት ማክኮኔል ከፍሎሪዳ ሪፐብሊካኑ ሪክ ስኮት የቀረበባቸውን ፈተና በማለፍ የሴኔት አናሳ ፓርቲ መሪ ሆነው በድጋሚ ተመርጠዋል።
ከኮንግረስ ውጭ ያሉ የምርጫ ውጤቶች ይፋ መደረጋቸውን ቀጥለዋል።
ካረን ባስ ቢሊየነሩን ሪክ ካሩሶን በማሸነፍ የሎስ አንጀለስ ከንቲባ እንደሚሆኑ ተገምቷል።
ዴሞክራቷ ኃላፊነቱን በመያዝ የመጀመሪያዋ ሴት እና የከተማዋ ሁለተኛ ጥቁር ከንቲባ ይሆናሉ።












