ቼልሲን ከ አርሰናል፤ ሊቨርፑልን ከ ቶተነሃም ያገናኘው የፕሪሚየር ሊግ ግምት

የቢቢሲው የፕሪሚየር ሊግ ውጤት ገማቹ ክሪስ ሱቶን የዘንድሮውን የሊግ ጨዋታ ውጤት በትክክል መገመት ፈተና ሆበት ቆይቷል።
በተለይ በተለይ ሊድስ እና በርንማውዝ የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች መገመት ከብዶት ቆይቷል። ታዲያ ሁለቱ ክለቦች ነገ ሲገናኙ ግምቱን ለማን ይሰጥ ይሆናል?
ቅዳሜ

ሊድስ ከ በርንማውዝ
“የሊድስ እና በርንማውዝ ደጋፊዎች በግምቶቼ ደስተኛ አይደሉም” የሚል ሱቶን፤ “በዚህም ሁለቱም ቢሸነፉ ደስ ባለኝ ነበር” ይላል።
በባለፈው ሳምንት ሊድሶች ወደ አንፊልድ ሲያቀኑ በሊቨርፑል 6 ለ 1 እንደሚሸነፍ ገምቶ ነበር። ሊድሶች ግን በአስደናቂ ብቃት ሊቨርፑልን በደጋፊው ፊት 2 ለ 1 አሸንፈዋል።
ሱቶን በርንዝማውዝ ባለፈው ሳምንት ቶተንሃምን 2 ለ 0 መምራት ቢችልም የመጨረሻው ፊሽካ ሲነፋ 3 ለ 2 መሸነፋቸውን አስታውሶ፤ በነገው ጨዋታ ሊድሶች የበላይነትን እንደሚይዙ ግምቱን ያስቀምጣል።
ግምት፡ 2 - 1
ማንችስተር ሲቲ ከ ፉልሃም
ሲቲ የፊት መስመር ተጫዋቹን ሃላንድን በጉዳት ሳያሳልፍ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች አድርጓል።
ይሁን እንጂ ሃላንድ ኖረም አልኖረ ሰማያዊዎቹ ይህን ጨዋታ በቀላሉ ያሸንፋሉ ይላል።
ሱቶን እርግጠኛ መሆን ያልቻልኩት ፉልሃም ከመሸነፍ የሚታደጋቸውን ጎል ማስቆጠር ይችላሉ ወይ የሚለው ነው።
ግብ ጠባቂው ኤደርሰን ስለሆነ ፉልሃም ጎል አያሰቆጥርም በሚለው እሄዳለሁ።
ግምት 3 – 0

ፎረስት ከ ብሬንትፎርድ
ኖቲንግሃም ፎረስት ባለፈው ሳምንት በአርሰናል 5 ለ 0 ከተሸነፈ በኋላ አሰልጣኝ ስቲቭ ኩፐር በቡድኑ ተፎካካሪነት ላይ ጥያቄን አንስቷል።
ኖቲንግሃም ፎረስቶች ከአርሰናል ጋር ከመጫወታቸው በፊት ሊቨርፑልን በሜዳቸው አሸንፈው ነበር። በሜዳቸው ብሬንትፎርድን ያሸንፋሉ ብዬ እንዳልገምት ባለፈው ሳምንት በአርሰናል በሰፊ የጎል ልዩነት መሸነፋቸው ጥርጣሬ ውስጥ እንድገባ አድርጎኛል።
ብሬንትፎርድ ደግሞ በውድድር ዘመኑ ከሜዳቸው ውጪ እስካሁን አላሸነፉም። በዚህም ሁለቱ ክለቦች በአቻ ውጤት ይለያያሉ ብዬ ገምታለሁ።
ግምት፡ 1 -1
ዎልቭስ ከ ብራይተን
ባለፈው ሳምንት ዎልቭስ ከብሬንትሮድ አንድ ነጥብ ይዘው ለመውጣት ትልቅ ትግል አድርገዋል። ዎልቭሶች ምንም እንኳ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ቢቀመጡም እንደ ቡድን ያላቸው አቋም ግን የተዳከመ ነው ብዬ አላስብም።
በሌላኛው ስሙ “በስጩ” ተብሎ የሚታወቀውም ዲዬጎ ኮስታን በቀይ ካርድ ቅጣት ማጣታቸው ስለሚጎዳቸው እና ከወቅቱ የብራይተን አቋም አንጻር ድሉ የብራይተን ይሆናል ብዬ ገምታለሁ።
ግምት፡ 0 - 1

ሌስተሮች አሁን በወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኙ እንጂ መሻሻሎችን እያሳዩ ይገኛሉ።
ባለፈው ሳምንትም ይሸነፉ እንጂ ሻምፒዮኖቹን ሲቲን ጥሩ አድርገው ፈትነዋል።
ቢሆንም ኤቨርተን በሜዳው ይህን ጨዋታ ያሸንፋል የሚል ግምት አለኝ። ኤቨርተን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ክሪስታል ፓላስን እንደረቱት ሁሉ ድልን በጉዲሰን ፓርክ ያጣጥማሉ ብዬ ገምታለሁ።
ግምት፡ 2 - 1
ቼልሲ ከ አርሰናል
ባለፈው የውድድር ዓመት አርሰናል ወደ ስታንፎርድ ብሪጅ ተጉዞ ሁለት ጊዜ አሸንፏል። ለሦስት ተከታታይ ጊዜ ግን ያሸንፋሉ ብዬ አልገምትም።
አርሰናል የማሸነፉ ጉዳይ የቡካዮ ሳካ ወደ ሜዳ መግባት ላይ የሚመረኮዝ ይሆናል።
ግርሃም ፖተር ወደ ቼልሲ ከመጡ ወዲህ ቡድኑ የተሻለ አቋም እያሳየ ነው። ባለፈው ሳምንት በብራይተን ያልተጠበቀ ሸንፈት ቢገጥመው ዳግም በአርሰናል ይሸነፋል ብዬ አልገምትም።
ግምት፡ 1-1
አስቶን ቪላ ከ ማንችስተር ዩናይትድ
ማንችስተር ዩናይትድ ከሜዳው ውጪ ድል ያመጣል ብዬ እገምታለሁ።
ኤሪክ ቴን ሃግ አስገራሚ ቡድን እየመሰረቱ እንደሆነ እገምታለሁ። ቪላ ባለፈው ሳምንት በኒው ካስል ተሸንፏል። ኡናይ ኤምሪን አሰልጣኝ አድርጎ ቢቀጥርም አሰልጣኙ በዩናይትድ መሸነፉ አይቀሬ ነው።
ግምት፡ 0 - 1

ሳውዝሃምፕተን ከ ኒውካስትል
ኤዲ ሃው በኒውካስል እያደረገ ያለው በጣም የሚወደድ ነገር ነው። ቡድኑ በሚገባ ተዋቅሯል። ሲከላከሉም ጠንካራ ናቸው።
ምርጥ አቋም እያሳየ የሚገኘው አጥቂያቸው ካለም ዊልሰን ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለዓለም ዋንጫ ወደ ኳታር መጓዝ አለበት ብዬ አምናለሁ።
ሳውዝሃምፕተኖች ደግሞ ወጥ የሆነ አቋም እያሳዩ አይደለም። ሁሌም የምለው ነገር ነው። ከፍ ዝቅ ይላሉ። ለምሳሌ ከአርሰናል ጋር በነበራቸው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ ተወስዶባቸው ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ድንቅ ነበሩ።
የሳውዝሃምፐተንን አቋም በየሳምንቱ መገመት ከባድ ነው። ኒውካስትል ዩናይትዶች በአንጻሩ ጥሩ አቋም ላይ ይገኛሉ። ስለዚህ ኒውካስል ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ያሸንፋል።
ግምት፡ 0 – 2
ዌሰት ሃም ከ ክሪስታል ፓላስ
ዘንድሮ ሊጉ ከተጀመረ ከሜዳው ውጪ እስካሁን ያላሸነፈው ቡድን ክሪስታል ፓላስ ነው። ፓትሪክ ቪዬራ ወደ ዌስት ሃም ሄዶም ይህን ሪከርዱን ይቀይራል ብዬ አልጠብቅም።
ዌስት ሃሞች ከማንችስተር ጋር በነበራቸው ጨዋታ ነጥብ ሳይጋሩ መውጣታቸው ዕድለ ቢስ ናቸው ያስብላል። ዌስት ሃሞች በሜዳቻው ለንደን ስታዲየም በሁሉም ውድድሮች ያደረጓቸውን 6 ተከታታይ ጨዋታዎች አሸንፈዋል።
ግምት፡ 2 – 1
ቶተንሃም ከ ሊቨርፑል
ሶን ሂዩግ-ሚን መጎዳት ለቶተነሃም አደጋ ነው። ሌሎቹ አጥቂዎች ሪቻርልሰን እና ኩሉሴቪስኪ በጉዳት እንደማይሰለፉ መዘንጋትም የለብንም።
ለቶተንሃም ደጋፊዎች መልካሙ ነገር ይህን ጨዋታ ሊቨርፑል ያሸንፋል ብዬ መገመቴ ነው። ምክንያቱም ሊቨርፑል ያሸንፋል ብዬ ስገምት ውጤቱ ተቃራኒ እየሆነ ስለመጣ።
እውነት ለመናገር ከዚህ ውጤት ምን መጠበቅ እንዳለብኝ እርግጠኛ አይደለሁም። ሊቨርፑል በአውሮፓ ጨዋታዎች ድንቅ ውጤት እያስመዘገበ፣ በፕሪሚየር ሊጉ ያልተጠበቀ ሽንፈት እያስተናገደ ነው። በሊድስ እና በኖቲንግሃም ፎረስት መሸነፋቸው ይታወሳል።
ስፐርሶች ደግሞ ሶን ኖረም አልኖረ፤ ቀድመው ቢመሩም፤ ፊሽካው እስኪነፋ ለማሸነፍ የማያደርጉት ጥረት የለም።
ይህን ጨዋታ ሊቨርፑል ያሸንፋል ብዬ ብገምትም ውጤቱ በተቃራኒው ሊሆን ይችላል።
ግምት፡ 1 – 2












