በዩኬ ጥንዶቹ ልጃቸውን ከመንግሥት ማደጎ ለማስመለጥ በሚል ሲጠፉ በመሞቷ በቸልተኝነት ግድያ ጥፋተኛ ተባሉ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
በዩናይትድ ኪንግደም ሁለት ጥንዶች ልጃቸውን ከመንግሥት ማደጎ ለማስመለጥ ሲሞክሩ በመሞቷ በከባድ የቸልተኝነት ግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ተባሉ።
የ38 ዓመቷ ኮንስታንስ ማርቲን እና የ51 ዓመቱ ማርክ ጎርደን ከረጅም እና የተወሳሰበ ሁለተኛ የክስ ሂደት በኋላ ሰኞ ዕለት የጥፋት ብይን ተላልፎባቸዋል።
ውሳኔው ቪክቶሪያ የተባለችውን የህፃን ልጃቸውን የበሰበሰ አስከሬን በዘንቢል ጥለው ከተገኙ ከሁለት ዓመታት በኋላ የተሰጠ ነው።
ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም በዋለው ችሎት የልጃቸውን መወለድ ባለማሳወቅ፣ ፍትህ እንዳታገኝ ሞቷን በመደበቅ እና በልጅ ጭካኔ ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
በከባድ ቸልተኝነት ግድያ ጥፋተኛ መባላቸው የጥንዶቹ ባህርይ በጣም መጥፎ እና አንድ ብቁ ወላጅ ማድረግ ካለበት የኃላፊነት ደረጃ የወረደ ነው ማለት ነው።
በዳግም ችሎቱ ዐቃቢ ሕግ ጥንዶቹ የልጃቸውን ደኅንነት ላለመጠበቅ ወስነው ነበር እና እርምጃቸው ሆን ተብሎ የተፈፀመ ነው በሚል ተከራክሯል።
የዐቃቢ ሕግ ክስ ዋነኛ ማጠንጠኛ በአውሮፓውያኑ ጥር 2023 ህፃኗ በሰውነት ሙቀት ማነስ (ሃይፖተርሚያ) ወይም በጠባብ፣ ቀዝቃዛ፣ እርጥበታማ እና ነፋሻማ በሆነ ከባቢ አንድ ላይ ስትተኛ ታፍና ሞታለች የሚል ነው።
እስካሁን ድረስ የጤና ባለሙያዎች የሞቷ ትክክለኛ ምክንያት ላይ እርግጠኛ አይደሉም።
ጥንዶቹ በአያያዛቸው ምክንያት እንደሌሎች ልጆቻቸው መንግሥት ቪክቶሪያን እንዳይነጥቃቸው ከሌሎች አራት ልጆቻቸው ጋር ይዘው መሸሸታቸው ተነግሯል።
በችሎቱ የሕፃኗ አባት ማርቲን ከሀብታም ቤተሰቦች የተገኘ እና የተሟላ አስተዳደግ እንደነበረው እንዲሁም እ.አ.አ በ1989 የ14 ዓመት ታዳጊ እያለ በፍሎሪዳ አሜሪካ በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ እንደነበር ተነስቷል።
በመጀመሪያ ክሱ ይህ ፍርድ ያልታወቀ ቢሆንም በሁለተኛው ዙር ክሱ ግን ይፋ ሆኗል።
ጥንዶቹ ፍርዱ ሲሰጣቸው ከመቀመጫቸው ለመነሳት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ጎርደን ከፍርዱ በኋላ ለዳኛው "ፍትኃዊ ያልሆነ ችሎት" ነው ያለ ሲሆን ይግባን ብሎ እንደሚያሸንፍ ተናግሯል።
የጥንዶቹ የፍርድ ቤት ጉዳይ ያልተለመደ ሲሆን፤ ከአዋኪነታቸው እና ተገማች ካልሆነው ባህሪያቸው ጀምሮ ፍርድ ቤት ባለመቅረብ ችሎቱ እንዲስጓተት አድርገዋል።
የዳኛውን ክብር ማጉደፍ፣ የፍርድ ቤት ሠራተኞችን መረበሽ እንዲሁም በችሎት መሀል ማውራት የመሳሰሉ እንግዳ ባህሪ አሳይተዋል።
ተከሳሾቹ ጠበቆቻቸውን ሲያባሩ አንዳንዶቹ ደግሞ በራሳቸው ውክልናቸውን ሲያነሱ ከመጀመሪያቸው ችሎት ጀምሮ 14 ጠበቆችን አቁመዋል።
ከብይኑ በኋላ አስተያየት የሰጡት ዋና ዐቃቢ ሕግ ጃስዋንት ናርዌል ተከሳሾቹ "ለትድርጊታቸው ትንሽ ፀፀት ብቻ" አሳይተዋል ያሉ ሲሆን፤ "የፍርድ ቤት ሂደቱን ለማደናቀፍ እና ለማዘግየት የተለያዩ ስልቶችን" ተጠቅመዋል ብለዋል።
"በዚህ አሳዛኝ ጉዳይ የተጎዱ ሰዎች በፍርዱ ፍትህ እና መፅናኛ ያገኛሉ ብየ ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉም አክለዋል።
ከፍተኛ ዐቃቢ ሕግ የሆኑት ሰማንታ ይልንድ በበኩላቸው ጥንዶቹ ለልጆቻቸውን በሚታይ አደጋ ማጋለጣቸው አስደንጋጭ እና በራስ ወዳድነት ላይ የተመሰረተ ግድየለሽነት ነው ብለዋል።
እ.አ.አ በ2023 ጥንዶቹ ለ53 ቀናት በፖሊስ ሲታደኑ ጉዳያቸው ትኩረት ስቧል። በቁጥጥር ስር ላለመዋል ከቤታቸው ውጭ በመተኛት እና ፊታቸውን መሸፈንን ጨምሮ ጥርጣሬ ውስጥ እንዳይገቡ እርምጃዎችን ወስደዋል።
እ.አ.አ የካቲት 27/2023 ጥንዶቹ ከተገኙ ከሁለት ቀናት በኋላ ልጃቸው ሞታ ተገኝታለች።
ፖሊስ የህፃኗ ሞት "ሙሉ ለሙሉ ሊወገድ የሚችል" ሲል ጥንዶቹ እርዳታ መጠየቅ ይችሉ ነበር ብሏል።












