ካማላ ሀሪስ በመጀመሪያ የምርጫ ቅስቀሳቸው ትራምፕን ሲወቅሱ ትራምፕ ደግሞ ምላሽ ሰጥተዋል

ካማላ ሀሪስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ በሚቀጥለው ምርጫ ፕሬዝዳንት ሆነው ለመወዳደር የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ጀምረዋል።

ካማላ በመጀመሪያው የምርጫ ቅስቀሳቸው ዶናልድ ትራምፕን የወቀሱ ሲሆን በሚቀጥለው ኅዳር የሚደረገው ምርጫ "በቀድሞዋ አቃቤ ሕግ እና በተፈረደበት ወንጀለኛ" መካከል የሚደረግ ነው ብለዋል።

በዊስኮንሲን ግዛት 3 ሺህ ገደማ ለሚሆኑ ደጋፊዎቻቸው ንግግር ያደረጉት ካማላ፤ ዶናልድ ትራምፕን እርሳቸው አቃቤ ሕግ ሳሉ እሥር ቤት ከወረወሯቸው አጭበርባሪዎች ጋር አመሳስለዋቸዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው ምክትል ፕሬዝዳንቷን በተመለከተ “ውሸታሟ ካማላ ሀሪስ የነካችው ሁሉ ድምጥማጡ ይጠፋል” ሲሉ በማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው ፅፈዋል።

የቀድሞ የካሊፎርኒያ ግዛት አቃቤ ሕግ፤ ካማላ ሀሪስ ከዲሞክራቲክ ተወካዮቻቸው ዕጩ መሆን የሚያስችላቸውን ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘታቸው በተሰማ በማግስቱ ነው ምርጫ ቅስቀሳ የጀመሩት።

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እሑድ አመሻሹን ከምርጫ ውድድሩ ራሳቸውን ማግለላቸውን አሳውቀው ምክትላቸው ካማላ ሀሪስ ለሚያደርጉት ቅስቀሳ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ማሳወቃቸው ይታወሳል።

ባይደን ባለፈው ሰኔ ከትራምፕ ጋር በነበራቸው ክርክር ያሳዩትን አቋም ተከትሎ ከበርካታ ዲሞክራቶች እና ገንዘብ ለጋሾች ጫና ሲደርስባቸው ነበር።

ከባይደን እና ከሌሎች የፓርቲው አባላት ድጋፍ ያገኙት ካማላ በ36 ሰዓታት ውስጥ 100 ሚሊዮን ዶላር ከለጋሾች ማግኘታቸው ብዙዎችን አስደንቋል።

ከዚህም ባለፈ ሮይተርስ የዜና ወኪል እና ኢፕሶስ በሰበሰቡት የሕዝብ ድምፅ መሠረት ካማላ ከተቀናቃኛቸው ትራምፕ 2 በመቶ ቀድመው በ42 በመቶ እየመሩ ነው።

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አዳራሽ በጭብጨባ ለተቀበላቸው ደጋፊ ንግግር ያደረጉት ካማላ የካሊፎርኒያ አቃቤ ሕግ ሳሉ የነበራቸውን ልምድ አጋርተዋል።

“ሁሉም ዓይነት ተንኳሽ አጋጥሞኛል። ሴቶችን የሚበድሉ፤ ደንበኞቻቸውን የሚያጭበረብሩ፣ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ሕግ የሚጥሱ። ለዚህ ነው እንደ ዶናልድ ትራምፕ ያሉ ሰዎችን አውቃቸዋለሁ የምለው” ብለዋል ካማላ።

ይህን ንግግር ሲያሰሙ ደጋፊዎቻቸው “ካማላ! ካማላ!” እያሉ አድምቀዋቸዋል። አንዳንድ ታዛቢዎች የካማላ ቅስቀሳ ባይደን ቅስቀሳ ሲያደርጉ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ደመቅ ያለ ነው ይላሉ።

የካማላ ደጋፊዎች የዶናልድ ትራምፕ ስም ሲነሳ “ሎክ ሂም አፕ” አሊያም “ወሕኒ ይውረድ” ሲሉ ድምፃቸውን አሰምተዋል። ዶናልድ ትራምፕ በ2016 የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የሂላሪ ክሊንተንን ስም ሲያነሱ ደጋፊዎች “ወሕኒ ትውረድ” ማለታቸው ይታወሳል።

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው ካማላ ሀሪስ በአሜሪካ ታሪክ ብዙ ተወዳጅ ያልሆኑ ምክትል ፕሬዝደንት ናቸው የሚል የሕዝብ ድምፅ ለጥፈዋል።

ካማላ በምርጫ ቅስቀሳቸው ቅድሚያ ሰጣቸዋለሁ ያሏቸውን ሐሳቦች ለደጋፊዎቻቸው ይፋ አድርገዋል። የጦር መሣሪያ ቁጥጥር፣ የፅንስ ማቋረጥ አገልግሎት፣ የሕፃናት ድኅነት ቅነሳ፣ የሠራተኞች ማሕበራት መብት እና ለሁሉም ተደራሽ የሆነ የጤና አገልግሎት ከተጠቀሱት ፖሊሲዎች መካከል ናቸው።

ካማላ ሀሪስ ይህን ድጋፍ ይዘው እስከ ምርጫው ድረስ ይዘልቃሉ ወይ የሚለው ግልፅ አይደለም።

ሪፐብሊካኖች ደግሞ ካማላ በምክትል ፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ብዙ ሥራዎችን አልሠሩም በማለት እያጣጣሏቸው ይገኛል።

ትራምፕ በወርሀ መስከረም ከባይደን ጋር ሁለተኛ ዙር ክርክር ለማድረግ ቀጠሮ ነበራቸው። ነገር ግን ከምክትል ፕሬዝደንቷ ጋር ቢሆንም ክርክር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።