ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቴክኒክ ችግር ምክንያት በአሜሪካ ተቋርጦ የነበረው የአገር ውስጥ በረራ መልሶ ተጀመረ
በአሜሪካ የአየር በረራ መቆጣጠሪ ሥርዓት ላይ አጋጥሞ በነበረ የቴክኒክ ችግር ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ የአገሪቱ ውስጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶች መልሰው እንዲጀመሩ ተደረገ።
የአሜሪካ ፌደራል የአየር ትራንስፖርት አስተዳደር እንዳለው፣ አብራሪዎች በበረራ መስመሮቻቸው ላይ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ አደጋ የሚያስከትሉ ክስተቶችን በሚጠቁመው ሥርዓት ላይ የቴክኒክ ችግር አጋጥሞ ነበር።
ጨምሮም የተፈጠረውን ችግር ለማስተካከል እና በረራዎች መልሰው እንዲጀመሩ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን፣ ይህም ሰዓታትን ሊወስድ እንደሚችል ባለሥልጣኑ የገለጸ ሲሆን አሁን በርካታ የአሜሪካ አየር ማረፊያዎች ሥራ ጀምረዋል።
የአየር ትራንስፖርት ባለሥልጣኑ ለሰዓታት የቆየው ችግር የተፈጠረው በርካታ በረራዎች በቁጥጥር ሥርዓቱ ላይ ባስከተሉት መጨናነቅ ሳቢያ ነው።
ይህ የቴክኒክ ችግር ከአገር ውስጥ በረራዎች ባሻገር ዓለም አቀፍ በረራዎች ላይ ምን ያህል ተጽእኖን ሊያስከትል እንደሚችል እስካሁን አልታወቀም።
ክስተቱን በተመለከተ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ማብራሪያ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ጽህፈት ቤታቸው ዋይት ሐውስም “በዚህ ሰዓት” ችግሩ በመረጃ መረብ ላይ ከተፈጸመ ጥቃት ጋር የተያያዘ መሆኑን የሚያመለክት ምንም አይነት መረጃ የለም ብሏል።
የዋይት ሐውስ የፕሬስ ክፍል ኃላፊ በትዊተር ገጻቸው ላይ ፕሬዝዳንት ባይደን በክስተቱ ዙሪያ “ሙሉ ምርመራ እንዲደረግ” ማዘዛቸውን አስፍረዋል።
ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካ አየር መንገድ እንዳሳወቀው የገጠመው የቴክኒክ ችግር “ሁሉንም አየር መንገዶች እና ሁሉንም በረራዎች” እንዲስተጓጎሉ ማድረጉን አመልክቷል።
ዩናይትድ ኤርላይን የተባለው አየር መንገድም ከአሜሪካ የአየር ትራንስፖርት አስተዳደር መረጃ እስከሚያገኝ ድረስ ሁሉንም የአገር ውስጥ በረራዎች እንዲዘገዩ ማድረጉን አሳውቆ ነበር።
በቴክሳስ ግዛት ውስጥ የሚገኘው የኦስቲን-በርግስትሮም ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በትዊተር ገጹ ላይ እንዳረጋገጠው፣ በአገሪቱ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ላይ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ምክንያት “በመላው አሜሪካ በሚገኙ አየር ማረፊያዎች ላይ የበረራ መስተጓጎል ተከስቷል” ብሏል።
ጨምሮም ባጋጠመው ችግር ምክንያት የሚነሱ እና የሚያርፉ መንገደኞች ላይ መዘግየት ሊኖር እንደሚችል ያሳሰበ ሲሆን፣ ተጓዦችም ከጉዟቸው እንደዘገዩ የሚገልጹ መረጃዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ሲያጋሩ ቆይተዋል።
የአሜሪካ መንግሥት የትራንስፖርት መሥሪያ ቤት ኃላፊ ፔት ቡቲዢዥ በበኩላቸው የተከሰተውን እክል በተመለከተ ከፌደራሉ የአየር ትራንስፖርት ባለሥልጣናት ጋር መነጋገራቸውን እንዲሁም ችግሩን “በፍጥነት እና በአስተማማኝ ሁኔታ” ለመቅረፍ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።