ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር የመቀመጫ ቀበቶ ባለማሰራቸው ተቀጡ
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ እየተጓዘ ባለ መኪና ውስጥ ሳሉ የመቀመጫ ቀበቶ ባለማሰራቸው ተቀጡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ ላይ ባለ መኪና ውስጥ ሆነው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለጠፍ ቪድዮ እየቀረጹ ሳለ የመቀመጫ ቀበቷቸውን ባለማሰራቸው መቀጣታቸውን ፖሊስ ገልጿል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ “ስህተት መሆኑን እናምናለን ይቅርታም እንጠይቃለን” ብሎ ቅጣቱን እንደሚከፍል አክሏል።
ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የመቀመጫ ቀበቶ ያላደረጉ ሰዎች 100 ፓውንድ ይቀጣሉ። ጉዳዩ ፍርድ ቤት ከደረሰ ቅጣቱ 500 ፓውንድ ሊደርስ ይችላል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቅጣት የተዳረጉት ስለ መንግሥታቸው ወጭ የሚገልጽ ቪድዮ መኪና ውስጥ ቀርጸው በኢንስታግራም ገጻቸው ባጋሩበት ወቅት ነው።
ሱናክ በ2020 ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር ቦሪስ ጆንሰን ጋር የኮቪድ ክልከላ በመጣስ የልደት ድግስ በመታደማቸው እሳቸውም ባለቤታቸውም ተቀጥተዋል።
የሌበር ፓርቲ ቃል አቀባይ “ሪሺ ሱናክ ለፎቶ ሲሉ የፈጸሙት ድርጊት መሳቂያ አደረጋቸው” ብለዋል።
ሊበራል ዴሞክራቶች በበኩላቸው “በፖሊስ ለመቀጣት ሁለተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ሕግ ግድ እንደማይሰጣቸው አሳይተውናል” ብለዋል።
የወግ አጥባቂው የምክር ቤት አባል ስኮት ቤንተን ግን “ሁሉም ሰው ይሳሳታል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተከላክለዋል።
“ፖሊስ ከባድ ወንጀሎችን ማስቆም ላይ ቢያተኩር ይሻላል። በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተመሳሳይ ቅጣት ይቀጣሉ” ሲሉም አክለዋል።
ከ14 ዓመት በላይ የሆኑ ተሳፋሪዎች የመቀመጫ ቀበቶ ማሰር ግዴታ አለባቸው።
ቅጣት የማይጣለው የመቀመጫ ቀበቶ ላለማሰር የሐኪም ማስረጃ ካለ፣ መኪናው ውስጥ ፖሊስ ወይም የእሳት አደጋ ሠራተኞች ካሉ ብቻ ነው።