ሶማሊያዊው የዓለም ዋንጫ ዳኛ አሜሪካ እንዳይገባ ታገደ

በዓለም ዋንጫ የመጀመሪያው ሶማሊያዊ ዳኛ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ኦማር አርታን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በዓለም ዋንጫ የመጀመሪያው ሶማሊያዊ ዳኛ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ኦማር አርታን
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በዓለም ዋንጫ የመጀመሪያው ሶማሊያዊ ዳኛ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ኦማር አርታን አሜሪካ እንዳይገባ ታገደ።

በአውሮፓውያኑ 2025 የካፍ የዓመቱ ምርጥ ዳኛ የተባለው ኦማር፤ ማያሚ አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሰ በኋላ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ ተከልክሏል።

ዳኛው አሁን ቱርክ የሚገኝ ሲሆን፤ አሜሪካ ለመግባት ባለመቻሉ ከዓለም ዋንጫ ዳኞች ዝርዝር ውስጥ ወጥቷል።

ዳኛው ለምን ወደ አሜሪካ እንዳይገባ እንደታገደ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት በኩል የተባለ ነገር ባይኖርም በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጉዞ እገዳ ከተጣለባቸው አገራት አንዷ ሶማሊያ ናት።

ፊፋ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ከተነጋገረ በኋላ ዳኛው በዓለም ዋንጫ እንደማይሳተፍ አስታውቋል።

"ኦማር አብዱልቃድር አርታን አሜሪካ እንዳይገባ በመከልከሉ የ2026 የዓለም ዋንጫን እንደማይዳኝ ፊፋ ያረጋግጣል" ሲል መግለጫ አውጥቷል።

ፊፋ በአዘጋጅ አገራት የቪዛ አሰጣጥ ሒደት ውስጥ "ጣልቃ እንደማይገባ" ገልጿል። ይህም የቪዛ ጉዳይን በሕግ ክርክር ለመፍታት መሞከርን ይጨምራል።

የዳኛው የቪዛ ሁኔታ እንደማይለወጥ የአሜሪካ ባለሥልጣናት መግለጻቸውን ፊፋ አክሏል።

"ከዚህ ቀደምም ፊፋ ባሰናዳቸው መርሃ ግብሮች እንደነበረው አዘጋጅ አገር ማን ቪዛ ያገኛል፣ ማን ወደ አገር ውስጥ መግባት ይችላል የሚለውን ይወስናል" ብሏል።

የሶማሊያ የጤና፣ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር አማካሪ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ዳኛው ሕጋዊ ሰነዶች ቢይዝም ወደ አሜሪካ እንዳይገባ ታግዷል።

ናይሮቢ የሚገኙ የሶማሊያ ኤምባሲ ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዳኛው በቪዛ ጥየቃ እና በጉዞ ወቅት መሰናክል እንዳይገጥመው የዲፕሎማት ፓስፖርት ተሰጥቶታል።

የሶማሊያ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ከፊፋ ማብራሪያ ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል።

የዋይት ሀውስ የዓለም ዋንጫ ጉዳዮች ግብረ ኃይል መሪ አንድሪው ጊሊያኒ "ክብረ ነክ የሆነውን ዝርዝር መረጃ መስጠት አልችልም፤ ነገር ግን የጉምሩክ እና ድንበር ጥበቃ ባለሥልጣን ውሳኔ ትክክል እንደሆነ እና እንደምደግፈው ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሶማሊያዊው ዳኛ ፊፋ ለዓለም ዋንጫ ከመረጣቸው 52 ዳኞች መካከል አንደኛው ነበር። ኦማር አርታን ከ2018 ጀምሮ የፊፋ ይፋዊ ዳኛ ሲሆን የአፍኮን ጨዋታዎችን ዳኝቷል።