ሩሲያ ወታደሮቿን ከዩክሬን ቁልፍ ከተማ ልታስወጣ ነው

የፎቶው ባለመብት, RUSSIAN DEFENCE MINISTRY
የሩስያ ጦር ከዩክሬኗ ኬርሶን ከተማ ለቆ እንዲወጣ ታዘዘ።
በዩክሬን የሩሲያ ጦር አዛዥ ጄኔራል ሰርጌይ ሱሮቪኪን ለከተማዋ ቁሳቁሶችን እያቀረቡ መቀጠል አይቻልም ብለዋል።
በዚህ ውሳኔ የሩሲያ ኃይሎች ከምዕራባዊው ዲኒፕሮ ወንዝ ዳርቻ ሙሉ በሙሉ ይወጣሉ ማለት ነው።
የዩክሬን የመልሶ ማጥቃት እያስተናገደች ላለችው ሩሲያ ይህ ትልቅ ጉዳት ነው።
የጦር ኃይሉ ከፍተኛ ባለስልጣን ውሳኔውን በሩሲያ የመንግስት ቴሌቪዥን ሲያሳውቁ፤ ጄኔራል ሱሮቪኪን ከኬርሶን ሆነው ሁኔታውን አሳውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ግን አልተሳተፉበትም። ዩክሬን ውስጥ ያልተሳካውን የሩሲያ ጦርነት የመሩት ዋናው መሐንዲስ መግለጫውን ለጄነራሎቹ የተተዉት ይመስላል።
በመስከረም ወር ሩሲያ ኬርሶንን ጨምሮ ሌሎች ሦስት ግዛቶችን ወደ ራሷ ግዛት እንደምትቀላቀል ያስታወቁት ፑቲን ነበሩ።
ጄኔራል ሱሮቪኪን በስብሰባው ላይ "አሁን ያለው አማራጭ መከላከያውን በዲኒፕሮ ወንዝ ላይ መከላከያ ማደራጀት ነው" ብለዋል።
የዲኒፕሮ ወንዝን ለመሻገር የተወሰደው ውሳኔ በዩክሬን ባለስልጣናት በጥንቃቄ እየታየ ነው።
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በረቡዕ ምሽት መግለጫቸው ኪዬቭ ውሳኔውን “በጣም በጥንቃቄ” አይታ እየተንቀሳቀሰች ነው ብለዋል።
"ጠላት ስጦታ አይሰጠንም። 'የበጎ ፈቃድ ሥራም' አያከናውንም። ሁሉንም እናሸንፋለን" ብለዋል።
"ስለዚህ ያለ ስሜታዊነት እና አደጋ ጉዳቱን ቀንሰን ሁሉንም መሬታችንን ነፃ ለማውጣት በጥንቃቄ እየተንቀሳቀስን ነው።"
ቀደም ሲል አማካሪያቸው ማይካሂሎ ፖዶሊያክ "ድርጊቶች ከቃላት የበለጠ ይናገራሉ" ሲሉ ተናግረዋል።
ሳምንቱን ሙሉ ሩሲያ ከኬርሶን እንደምትወጣ የሚገልጹ ሪፖርቶች ሲናፈሱ ነበር። በኬርሶን ዙሪያ ያሉ የዩክሬን ወታደሮችን ጠላት ወጥመድ ውስጥ ሊያስገባቸው እየሞከረ እንደሆነ ተናግረዋል ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩክሬን አዛዥ ጥሩ የስለላ መረብ እንዳላቸው እና በጥንቃቄ ብቻ እንደሚራመዱ ተናግረዋል ።
ከሩሲያ ውሳኔ በኋላ በኬርሶን ያሉ ሲቪሎች ከሩሲያ ጦር የሆኑ የቺቺን ወታደሮች በከተማው ካፌ እና ጎዳናዎች እየተዘዋወሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
ሌላ ግለሰብ ደግሞ "ሲታይ ምንም ነገር አልተለወጠም። በኬርሶን ቀኝ በኩል የማይታዩ ሲሆን ለብዙ ቀናትም አልነበሩም። የሚችሉትን ሁሉ ወስደዋል” ብለዋል።
ኦልጋ የተባሉ ሌላዋ የኬርሶን ከተማ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በከተማዋ ጥቂት ወታደሮች ብቻ ይታያሉ።
"በዚህ ወረራ እየተሰቃየሁ ነበር ነገር ግን ኬርሰን መልቀቅ ፍትሃዊ አይደለም ብዬ ስለማስብ እዚሁ ቀረሁ።
እዚህ መቆየት እና ሁሉም ችግሮች ማሸነፍ ነበረብኝ። ያጋጠመኝ ፈተና እንደሆነ አሰብኩ። ወደ ማብቂያው በመምጣቴ ደስተኛ ነኝ" ብለዋል።
የፕሬዚዳንት ፑቲን አጋሮች ውሳኔውን በደስታ ተቀብለዋል።
የዋግነር ቅጥረኛ ቡድን መስራች እና የረዥም ጊዜ የፑቲን ደጋፊ የሆኑት ዬቭጌኒ ፕሪጎዚን ውሳኔው “የአሸናፊ እርምጃ ባይሆንም፣ መጨነቅ ሳይሆን መደምደሚያ ላይ መድረስ እና ስህተቶች ላይ መሥራት አስፈላጊ ነው” ብለዋል።
"[የጄኔራል] ሱሮቪኪን የወሰደው ውሳኔ ቀላል አይደለም። ነገር ግን ኃላፊነትን እንደማይፈራ ሰው ወስኗል። በተደራጀ መልኩ ያለ ፍርሃት የውሳኔ አሰጣጡን በራሱ ላይ ወስዷል" ብለዋል።
በፑቲን ተመረጡት የቺቺኑ መሪ ራምዛን ካዲሮቭ በውሳኔው ጄኔራል ሱሮቪኪን "እንደ እውነተኛ ወታደራዊ ጄኔራል እንጂ ትችትን አልፈራም" ብለው ገልጸዋል።
እርምጃው በዩክሬን በተለይም በማህበራዊ ድር አምባዎች ላይ በርካቶች በደስታ ተቀብለውታል። አንዳንዶች ደግሞ ሲቀልዱበት ታይተዋል።
የኔቶ ዋና ጸሐፊ የንስ ስቶልተንበርግ ዩክሬን መራመድ ስትችል ማየት አበረታች ነው ብለዋል።
"ድሉ...የጀግኖቹ እና ደፋሮቹ የዩክሬን ወታደሮች ነው። በዚህ ውስጥ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከኔቶ አጋሮች የሚያገኙት ድጋፍም አስፈላጊ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
ጦርነቱ እንደተጀመረ የሩስያ ወታደሮች ደቡባዊ ዩክሬንን በኃይል ከተቆጣጠሯት ክሪሚያ ተነስተው ለመቆጣጠር የቻሉት በመጋቢት ወር ነበር።












