ፈረንሳይ በማሕበራዊ ሚድያ ሐሰተኛ ምርት የሚያስተዋውቁ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን የሚቀጣ ሕግ አወጣች

ታትሟል

ፈረንሳይ በማሕበራዊ ሚድያ ገፆቻቸው ለበርካታ ተከታዮቻቸው ሐሰተኛ ምርቶች የሚያስተዋውቁ ሰዎች ላይ ዘመቻ ከፍታለች።

እኒህ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለበርካታ ሺህ ተከታዮቻቸው የካንሰር ፈውስን ጨምሮ ሌሎች ሐሰተኛ ምርቶችን ያስተዋውቃሉ።

ፈረንሳይ አዲስ ያወጣችው ሕግ አደገኛና አሳሳች ምርት የሚያስተዋውቁ ሰዎች የገንዘብ ቅጣትና የሁለት ዓመት እሥር ይጠብቃቸዋል ይላል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጣውን ሐሰተኛ ምርት ማስተዋወቅ ለመግታት መንግሥት ብቻ ሳይሆን ግለሰቦችም ዘምተዋል።

የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ኦድሪ የኢንስታግራም ገፅ ከፍታ እኚህን ሰዎች እያጋለጠች ነው።

አንድ ‘ሪያሊቲ ቲቪ’ ላይ የሚታወቅ ግለሰብ የካንሰር ሴሎችን ያድናል ያለውን ምርት ሲያስተዋውቅ ስትመለከት ነው ወደዚህ ሥራ የገባችው።

በተፅዕኖ ፈጣሪዎች የተጨበረበሩ ሰዎችን ለማገዝ የተቋቋመ አንድ ድርጅት አንዳንድ ሰዎች ከተታለሉ በኋላ ራሳቸውን ለማጥፋት ቃጥተዋል ይላል።

“ሰዎች ትዳራቸውን ፈተዋል፤ ቤታቸውን አጥተዋል፤ ሥራቸውንም እንዲሁ፤ ለድባቴ ተዳርገዋል” ሲሉ አቪ ኮሌክቲች የተሰኘው ድርጅት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

የፈረንሳይ ፓርላማ አባሉ አርተር ዴላፖርቴ በዚህ ማጭበርበር ዘዴ ምክንያት ሰዎች እስከ 43 ሺህ ፓውንድ ድረስ አጥተዋል ይላሉ።

“ይህ ሕግ ለተጭበረበሩ ሰዎች የወጣ ነው፤ ባለሥልጣናትን ለማሳወቅ ለሠሩ ዜጎች የወጣ ነው” ሲሉ ለላይኛው የፈረንሳይ ምክር ቤት ተናግረዋል።

ኦድሪ፤ ይህ ጉዳይ ሃገራዊ የጤና ቀውስ ነው ትላለች።

“ሰዎች ሕመም ላይ ሲሆኑ የሆነ የሚያድናቸው ነገር እንዳለ ያስባሉ። ተጨማሪ ምግብ ከካንሰር ያድነናል ብለው መድኃኒት መውሰድ ሲያቆሙ ሊብስባቸው ይችላል።”

ነገር ግን ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ለቅሞ ማጋለጥ ቀላል ሥራ አይደለም።

ባለፈው ዓመት አንድ ክሪፕቶ ጉቭ የተሰኘ ስም ያለው የዩቲዩብ ገፅ 300 ሰዎችን አጨበርብሮ 4 ሚሊዮን ዩሮ ይዞ እንደጠፋ ሕግ አውጭው ኦሪሊዬን ታሼ ይናገራሉ።

ክሪፕቶ ጉቭ፤ ክሪፕቶከረንሲ ላይ እንዴት ወጭ ፈሰስ ማድረግ ይቻላል የሚል ሐሰተኛ መመሪያ ሰጥቶ ሰዎች እንዲያምኑት በማድረግ ነው ያጭበረበረው።

ሌላኛው ፈረንሳይ ውስጥ በጣም ታዋቂ የነበረው የማጭበርበር ሂደት ሥራ ለሚፈልጉ ሰዎች 500 ዩሮ እንሰጣለን ሲል የጀመረው ነው።

ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ይህንን ሥልጠና እንዲያስተዋውቁ ጉርሻ ተሰጥቷቸው ነበር።

የፈረንሳይ የኢኮኖሚ ሚኒስቴር እንደሚለው በዚህ የማጭበርበር ዘዴ ምክንያት 43 ሚሊዮን ዩሮ ጠፍቷል።

ሰዎች ዕቃ አዘው ሳይመጣላቸው ይቀራል፤ ለመዝናናት ቲኬት ቆርጠው፤ ሆቴል ተከራይተው ይታለላሉ፤ የተከለከ ነገር ያዘለ ሻምፑ ገዝተው ፀጉራቸውን ያጣሉ።

በ2023 በተሠራ ጥናት ከ60 ተፅዕኖ ፈጣሪዎች መካከል 60 በመቶው ምርቱን ሳያጣሩ የሚያስተዋውቁ ናቸው።

አሁን መንግሥት እርምጃ እየወሰደ ነው። አንዳንድ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ሐሰተኛ ምርትና አገልግሎት ስላስተዋወቁ መቀጣታቸውን የሚያሳይ ፅሑፍ እንዲለጥፉ በመንግሥት ተገደዋል።

2.2 ሚሊዮን ተከታዮች ያሉት ኢላን ካስትሮኖቮ በኢንስታግራም ገፁ ቁማርና ሐሰተኛ ሥልጠና ማስተዋወቁን እንዲያምን ተደርጓል።

የቀድሞ የሪያሊቲ ቲቪ ኮከብ የነበረችው ማየቫ ጌናም በአዲሱ ሕግ እንደምትስማማ ለ3.3 ሚሊዮን ተከታዮቿ ገልጣለች።

አሁን ጥያቄው የፈረንሳይ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ከአዲሱ ሕግ ጋር እንዴት ይታረቃሉ የሚለው ነው።