ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን በምርቶቹ ላይ ለቀረበበት ክስ 9 ቢሊዮን ዶላር ሊከፍል ነው

ታትሟል

ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ከምርቶቹ መካከል አንዱ የሆነው የሕጻናት ፓውደር እና በታልክ የሚሰሩ ምርቶቹ ካንሰር አስከትለዋል በሚል በሰሜን አሜሪካ የቀረቡበትን በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ክሶች እልባት ለመስጠት ወደ 9 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለመክፈል ማቀዱን አስታወቀ።

የውበትና ጤና መጠበቂያ ምርቶች አምራቹ ኩባንያ፣ የቀረቡበት ክሶች እስካሁን ስህተት መሆናቸውን ቢያምንም፣ ለመክፈል ያቀደው ገንዘብ የቀረቡበትን ሕጋዊ ጥያቄዎች እንደሚቋጩለት ተስፋ አድርጓል።

ድርጅቱ አሁን ላይ ለመክፈል ያስቀመጠው ገንዘብ ከዚህ ቀደም ለመክፈል አቅዶ ከነበረው 2 ቢሊዮን ዶላር ከአራት እጥፍ በላይ ነው።

ገንዘቡም ምርቶቹ የጤና ችግር አስከትሎብናል የሚሉ ሰዎችን ለመደገፍ ይውላል ብሏል።

ድርጅቱ ምርቱ ካንሰር የሚያመጣ 'አስቤስቶስ' ንጥረ ነገር ይዟል የሚሉትን ጨምሮ ታልክ [በዋናነት በማግኒዚየም፣ ሲሊከንና ኦክስጅን የተቀመመ] ሚኒራል ላይ የተመሠረቱት የሕጻናት ፓውደሮች ካንሰር አስከትሎብናል ካሉ የቀድሞ ደንበኞቹ ከ40 ሺህ በላይ ክሶች ቀርበውበታል።

በዚህም እንደ አውሮፓውያኑ 2020 'ሐሰተኛ መረጃዎቹ' በቆዳ ላይ የሚከሰት ሽፍታን ለመከላከል የሚረዱ እና ደረቅ ሻምፖን ጨምሮ ሌሎች የውበት መጠበቂያ ምርቶቹን ተፈላጊነት ቀንሶታል በሚል በታልክ የሚሰራውን ፖውደሩን በአሜሪካ መሸጥ አቁሟል።

ባለፈው ዓመትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሽያጭ ሊያቆም እንደሆነ አስታውቆ ነበር።

እዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊትም ኩባንያው የሕጻናት ፓውደርን ለ130 ዓመታት ሸጧል።አሁንም 'ኮርንስታርች' የተባለ ንጥረ ነገር ያለውን ተመሳሳይ ምርት መሸጡን ቀጥሏል።

ኩባንያው የቀረቡበትን ክሶች ለመፍታት ከ2021 ጀምሮ እየሞከረ ነው።

ይሁን እንጂ ቀደም ብሎ የንግድ ድርጅቶች ኪሳራን የሚመለከተው ፍርድ ቤት ያሳለፈበትን ውሳኔ ተከትሎ ኪሳራ ውስጥ ገብቷል።

የዓለም አቀፉ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የሕግ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚደንት ኤሪክ ሃስ “ ድርጅቱ አሁንም እነዚህ ክሶች ሐሰተኛ እንደሆኑና ሳይንሳዊ ማስረጃዎች ላይ ያልተመሠረቱ መሆናቸውን ያምናል” ብለዋል።

ይሁን እንጂ "ይህንን ችግር በሕግ ሥርዓት ለመፍታት አስርት ዓመታትንን ሊወስድ ይችላል።ድርጅቱንና የድርጅቱን ሥርዓት ለከፍተኛ ወጪ ይዳርጋል" ያሉት ምክትል ፕሬዚደንቱ፣ በዚህም በምርቱ ላይ ቅሬታ ያቀረቡ አብዛኞቹ ሰዎች ካሳ እንደማያገኙ ተናግረዋል።

"በመሆኑም ጉዳዩን በቀረበው እቅድ መሠረት መፍታት ውጤታማ ነው።ከሳሾቹንም በጊዜ ካሳ እንዲያገኙ ማድረግ ያስችላል እንዲሁም ድርጅቱን የሰዎች ጤና ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት ምርቶቹን ማምረት ላይ ትኩረት ማድረግ ይችላል” ብለዋል።

ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የታልክ ምርቶቹን በተመለከተ የቀረቡበትን ክሶች አብዛኞቹን ረትቷል፤ነገር ግን 22 ሴቶች ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ እንዲከፈላቸው በፍርድ ቤት የተላለፈውን ውሳኔን ጨምሮ በተወሰኑ ክሶች ላይ ተሸንፏል።

ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን በአዲሱ እቅድ አሁን ላይ ያሉ ወደ 60 ሺህ የሚጠጉ ከሳሾችን መደገፍ ይጠበቅበታል።