ሃሪ እና ሜጋን መርክል የዩኬ ቤታቸውን እንዲለቁ ተነገራቸው

ታትሟል

የሰሴክስ መሳፍንቶች ሃሪ እና ሜጋን መርክል በብሪታንያ ከሚገኘው ቤታቸው እንዲወጡ መጠየቃቸውን የጥንዶቹ ቃለ አቀባይ ተናገሩ።

ሃሪ እና ሜጋን መርክል እንዲለቁ የተነገራቸው በዊንድሶር ቤተመንግሥት ከሚገኘው ቤታቸው ነው።

ቤታቸው ለዮርኩ መስፍን እንዲሰጥ መወሰኑ ከዚህ ቀደም ተዘግቦ ነበር።

የልዑል ሃሪ እና የሜጋን ቃለ አቀባይ ዜናውን ቢያረጋግጡም ቤኪንግሃም ፓላስ በጉዳዩ ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።

ሃሪ እና ሜጋን ከሁለት ልጆቻቸው አርቺ እና ሊሊቤት ጋር በአሜሪካ፣ ካሊፎርኒያ ይኖራሉ።

ከሶስት ዓመታት በፊት የንጉሳውያን ህይወት ይቅርብን ብለው እንግሊዝን ለቀው መውጣታቸው ይታወሳል።

በበርክሸር በሚገው ዊንድሶር ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚገኘው ፍሮግሞር የተሰኘው ቤታቸው 10 መኝታ ክፍሎች ያሉት ሶሆን ለጥንዶቹ ከሟቿ ንግሥት ኤልዛቤት የተበረከተ ስጦታ ነበር።

ልዑል ሃሪ እና ሜጋን በንጉሳውያኑ ባለቤትነት ስር ያለው ቤታቸውን በአውሮፓውያኑ 2018/19፣ 2.4 ሚሊዮን ፓውንድ አውጥተው እድሳት አድርገውለታል። ወጪው መጀመሪያ በግብር ከፋዮች ተሸፍኖ የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን ልዑል ሃሪ ራሱ ከፍሏል።

ሃሪ እና ሜጋን በበኪንግሃም ቤተመንግሥት እንዲወጡ የተነገራቸው ‘ስፔር’ የተሰኘው አወዛጋቢ ማስታወሻዎችን ሃሪ ካሳተመ በኋላ ነው።

ከወራት በፊት ለህትመት የበቃው ይህ መጽሃፍ ኢ-ልብወለድ ባልሆኑ መጽሃፎች ዘርፍ ከፍተኛ ሽያጭ በማስመዝገብ ክብረ ወሰን ጨብጧል። ሃሪ በዚህ ማስታወሻው ላይ ወንድሙ አካላዊ እንዳደረሰበት እና ሌሎች አነጋጋሪ መረጃዎችን ይፋ አድርጓል።

የሟቿ ንግሥት ኤልዛቤት ሁለተኛ ልጅ አንድሪው በአቅራቢያው 31 መኝታ ክፍሎች ባሏቸው ቤት ውስጥ ይኖራል።

በአውሮፓውያኑ 2019 አንድሪው ቨርጂኒያ ጂፍሬ በተባለች ሴት ላይ ወሲባዊ ጥቃት አድርሷል የሚል አወዛጋቢ ዘገባን ተከትሎ ከንጉሳዊ ተግባራት እንዲገለል ተደርጓል። አንድሪው ክሱን ውድቅ ቢያደርግም ባለፈው ዓመት ቨርጂኒያ በአሜሪካ ያቀረበችውን ክስ እንድትተው ያልተገለጸ ገንዘብ መክፈሉ ተነግሯል።

በቅርብ ሳምንታት የወጡ ዘገባዎች ንጉሱ የአንድሪውን ዓመታዊ በጀት እንዲቀነስ ሃሳብ ማቅረባቸውን ተከትሎ የቤቱን ወጪዎች መሸከም እንደማይችል ተገልጿል።