ዩክሬን ከጦር ወንጀለኞች ጋር አልደራደርም አለች

ታትሟል

ጦርነቱን ለማስቆም ዩክሬን ከሩሲያ ጋር መደራደር የማይታሰብ ነው ሲሉ የአገሪቷ ከፍተኛ አቃቤ ህግ ለቢቢሲ ተናገሩ።

የዩክሬን መሪዎች በድርድር ላይ ያላቸውን አቋም እንዲያለዝቡ የአሜሪካ ባለስልጣናት ማበረታታቸውን በቅርቡ የአሜሪካ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ነገር ግን የዩክሬን ከፍተኛ አቃቤ ህግ አንድሪ ኮስቲን ሩሲያ ለጀመረችው ጦርነት ተጠያቂ መሆን አለባት ብለዋል።

አቃቤ ህጉ ልዩ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለማቋቋም ያላቸውን ፍላጎት አሳውቀው የሩሲያ ንብረቶችን በመውረስ ለጦርነቱ ማካካሻ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ጦርነቱ በዩክሬን ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ መንገዶች ስቃይ እያስከተለ ነው የሚለውን ስጋት ብዙም አይቀበሉትም።

"በርካቶች የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚን ፑቲን  ዩክሬን ላይ በፈጸሙት ጥቃት እየተሰቃዩ ነው" ያሉት ኮስቲን ሆኖም

“ከዩክሬን ውጭ ያሉ ሰዎች የሚሳኤል ድምፅ አይሰሙም። ስለሚፈነዳው ቦምብ አያውቁም። እየተፈጸመ ስላለው የዘፈቀደ ግድያ፣ መደፈር፣ ዘረፋም አያውቁም” ብለዋል።

አውሮፓውያን ለምግብ እና ለነዳጅ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ መሆኑን ቢያምኑም ነገር ግን "ዩክሬናውያን ለተመሳሳይ ትግል በህይወታቸው እየከፈሉ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

ሆኖም “ምንም አይነት ድርድር የማስቀጠል ጉዳይ የሚቻል አይመስለኝም" ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከወረራው የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ጀምሮ በሩሲያውያን እና በዩክሬናውያን መካከል ምንም ዓይነት የሰላም ድርድር የለም።

ሆኖም ሁለቱም ወገኖች በተባበሩት መንግስታት አማካኝነት ከዩክሬን ወደ ሌሎች አገራት እህል እንዲወጣ ስምምነት በሐምሌ ወር ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

ምንም እንኳን ኮስቲን ሩሲያውያን በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲዳኙ ፍላጎት ቢኖራቸውም ተንታኞች አስቸጋሪ እንደሆነ ያምናሉ።

ዩክሬንም ሆነ  ሩሲያ የአለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤትን ያቋቋመውን የሮም ስምምነት አልፈረሙም።