ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዶናልድ ትራምፕ
ታትሟል

ዶናልድ ትራምፕ ከፍሎሪዳ ወደ ኒው ዮርክ ሺህ ጊዜ ተመላልሰዋል። ቤታቸው ፍሎሪዳ-ሥራቸው ኒውዮርክ በመሆኑ።

የትናንቱ ግን ልዩ ነበር። በታሪክ የሚመዘገበው ይህ ጉዞ ለፖሊስ እጅ ለመስጠት ያደረጉት ጉዞ በመሆኑ ነው።

በአሜሪካ ታሪክ በወንጀል የተከሰሱ የመጀመርያው ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።

ትናንት ቀትር ላይ ፍሎሪዳ ከሚገኘው የተንጣለለው መኖርያ ግቢ ማሮላጎ ተነስተው ወደ ፓልም ቢች አየር መንገድ አውሮፕላን ተሳፍረዋል።

በግል አውሮፕላናቸው የሦስት ሰዓት በረራ ካደረጉ በኋላ ኒው ዮርክ ላጎርዲያ አየር መንገድ አርፈው፣ ማንሃታን ወደሚገኘው የግል ሕንጻቸው ገብተዋል።

ምሽቱን በትራምፕ ታወር ከጠበቆቻቸው ጋር እየመከሩ ያመሻሉ።

ዛሬ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ቀትር አካባቢ፣ በኒውዮርክ ንጋት ላይ ወደ ፍርድ ቤት ያመራሉ ተብሏል።

የኒውዮርክ ከንቲባና የጸጥታ አካላት ምናልባት በማንሃተን ሊፈጠር የሚችል አመጽ ካለ በሚል ሰፊ ዝግጅት እንደተደረገ መግለጫ ሰጥተዋል።

ትራምፕ ከፍሎሪዳ ማሮላጎ ግቢ ሲወጡና ፓ’ም ቢች አየር መንገድ እስኪደርሱ ድረስ መጠነኛ ደጋፊዎቻቸው ጎዳና ወጥተው አሸኛኘት አድርገውላቸዋል።

ኒውዮርክ ሲደርሱም በትራምፕ ታወር ደጃፍ መጠነኛ ድጋፍና አይዞህ ባይነት ተከታዮቻቸው አሳይተዋቸዋል።

እርሳቸውም ፊታቸው ሳይፈታ እጃቸውን በማውለብለብ ለደጋፊዎቻቸው ሰላምታን ሰጥተዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ የቀረበባቸው ክስ ይነበብላቸዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ለፕሬዝዳንትነት በተወዳደሩበት ዋዜማ ከወሲብ ተዋናይት ስቶርሚ ጋር ምሥጢር አታውጪብኝ በሚል ከፈሉት በተባለው ገንዘብ እና ገንዘቡን ለማወራረድ ያቀረቡት ምክንያት ለዚህ የወንጀል ክስ ዳርጓቸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጉዳያቸውን ሲመለከት የነበረው ገለልተኛ የፍርድ ሸንጎ (Grand Jury) ሰውየው በወንጀል እንዲከሰሱ ድምጽ ከሰጠ በኋላ ነው ትራምፕ እጅ ለመስጠት ወደ ኒውዮርክ የመጡት።

ለወሲብ ተዋናይት ገንዘብ መክፈላቸው በራሱ ወንጀል ባይሆንም ገንዘቡ ለሕግ አገልግሎት ነው የዋለው ብለው መዋሸታቸው ከተረጋገጠ ግን ወንጀል ሆኖ ሊያሳስራቸው ይችላል።

ሪፐብሊካኖች ይህ ክስ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ነው ይላሉ።

የ76 ዓመቱ ዶናልድ ትራምፕ በሁለት ዓመት ውስጥ በድጋሚ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለመሆን ራሳቸውን የሪፐብሊካን እጩ ለማድረግ ከፍተኛ የፖለቲካ ሥራ በሚሠሩበት ሰዓት ነው ይህ የወንጅል ክስ የቀረበባቸው።

ትራምፕ ከፍሎሪዳ ከመነሳታቸው በፊት ትሩ ሶሻል በተባለው ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ “ንጽሕ ሰውን በሐሰት ወንጅሎ ማሳደድ” የሚል ሐሳብ ብቻ ጽፈዋል።

ዛሬ የሚጠበቀው ትልቁ ነገር ሰውየው በካቴና ይታሰራሉ ወይ የሚለው ነው። ይህ ከሆነ ለተቀናቃኞቻቸው ትልቅ ድል ነው የሚሆነው። ምሥሉን ለዓመታት ከብዙዎች የአእምሮ ጓዳ ሊቀር የሚችል ይሆናል።

ትራምፕ ከኒውየርክ ጎዳና ወደ ሎወር ማንሃታን የፍርድ ቤት ግቢ ሲሄዱ ፎቶ ለማንሳት የዓለም ሚዲያ ከወዲሁ ቦታ ቦታውን ይዞ እየተጠባበቀ ነው።

ትራምፕ ፍርድ ቤት ከደረሱ በኋላ እንደማንኛውም ተጠርጣሪ ወንጀለኛ አሻራ ሰጥተው ግድግዳ ተደግፈው ፎቶ ይነሳሉ ወይ የሚለውን ሌላ ሲያነጋግር የቆየ ጉዳይ ነው።

ክሳቸው በኒውዮርክ አቆጣጠር ልክ ከቀኑ 8፡15 ሲሆን ይነበብላቸዋል።

ቀጥሎ ጥፋትዎን ያምናሉ ወይስ አያምኑም የሚል ጥያቄ የሚቀርብላቸው ሲሆን ትራምፕ ጥፋተኛ አይደለሁም ብለው ይናገራሉ።

ከዚህ በኋላ ነው የፍርድ ሂደቱ በዝርዝር የሚታየው።

ዶናልድ ትራምፕ በ2016 ምርጫ ተፍ ተፍ በሚሉበት ሰሞን እንቅፋት እንዳትሆንባቸው ለወሲብ ተዋናይት ስቶርሚ ዳኒኤልስ “ስለነበረን ነገር ትንፍሽ እንዳትይ” በሚል አፍ ማስያዣ 130ሺህ ዶላር ገንዘብ ዝውውር ያደረጉት በቀድሞ ጠበቃቸው ማይክል ኮህን በኩል ነበር።

ነገር ግን ስለገንዘቡ ሲጠየቁ ይህ ገንዘብ ለሕግ አገልግሎት የዋለ ነው ብለው አስተባብለዋል።

ስቶርሚም ሆነች ጠበቃው ግን በእርሳቸው ላይ ለመመስከር ዝግጁ ሆነዋል።

ትራምፕ ገንዘቡን አልሰጠሁም ከሴትዮዋም ጋር ወሲባዊ ግንኙነት አልፈጸምኩም ብለዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ላይ ከዚሁ ጋር ተያይዞ 30 ክሶች ይቀርቡባቸዋል።

የፍርድ ሒደቱ ለሕዝብ በቀጥታ ይተላለፋል ወይ የሚለው እስከ ትናንት ድረስ ሲያነጋግር የነበረ ሲሆን ዳኛ ጁዋን መርቻን ግን የፎቶ ካሜራ እንጂ የቀጥታ ሥርጭት እንደማይኖር ተናግረዋል።

የፎቶግራፍ ጋዜጠኞችም ቢሆን ፎቶዎችን ማንሳት የሚችሉት ፍርድ ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ነው ብለዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ሂደት በኋላ የዋስ መብታቸው ተጠብቆላቸው ምሽቱን ወደ ፍሎሪዳ ማሮላጎ ግቢ እንደሚያቀኑ ይጠበቃል።