በርካታ ሰዎችን የገደለው ጃፓናዊ በስቅላት ተቀጣ

ቶሞሂሮ ካቶ

የፎቶው ባለመብት, STR/AFP VIA GETTY IMAGES

ታትሟል

እአአ በ2008 ጃፓን፣ ቶኪዮ ውስጥ ሰባት ሰዎችን የገደለውን የ39 ዓመት ግለሰብ ጃፓን በሞት መቅጣቷን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ቶሞሂሮ ካቶ በአገሪቱ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስደንጋጭ ከሆኑት የጅምላ ግድያዎች አንዱን ፈጽሟል።

በወቅቱ 25 ዓመቱ የነበረው ግለሰብ በአኪሃባራ የገበያ ስፍራ የተሰበሰቡ እግረኞችን በጭነት መኪና ገጭቶ ሦስት ሰዎችን ገድሏል።

ተጨማሪ መንገደኞችን በጩቤ ወግቶ አራቱን ገድሎ ስምንት ደግሞ አቁስሏል።

ድርጊቱ በወቅቱ በጃፓን ማኅበረሰብ ውስጥ ስለ ዘፈቀደ ግድያ፣ ስለ በይነ መረብ ተጽዕኖ እና ስለ ወጣቶች የአእምሮ ጤና ድጋፍ አለመስፋፋት ሰፊ ክርክር አስነስቷል።

የጃፓን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፣ አሁን 39 ዓመት የሞላው ካቶ በቶኪዮ እስር ቤት በስቅላት ተቀጥቷል።

በዚህ ዓመት በአገሪቱ የሞት ቅጣት የተፈጸመበት የመጀመሪያው ግለሰብ ሆኗል።

ባለፈው ታኅሳስ ሦስት ሰዎች በስቅላት ተቀጥተዋል። ከ100 በላይ የሞት ፍርደኞች ውሳኔው እስኪተገበር በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

ጥቃቱ የደረሰበት ስፋራ

የፎቶው ባለመብት, STR/AFP VIA GETTY IMAGES

ካቶ ግድያ ከተፈፀመ በኋላ የስለት መሣሪያ ባለቤትነትን የሚመለከቱ ሕጎች ጥብቅ ሆነዋል።

የቶኪዮ አውራጃ ፍርድ ቤት ነበር በ2011 የሞት ፍርድ የወሰነበት።

የሞት ፍርዱን ለመቀልበስ በ2015 ይግባኝ ጠይቆ ተቀባይነት አጥቷል።

የሞት ፍርድን ከሚተገብሩ ጥቂት ያደጉ አገራት መካከል አንዷ ጃፓን ናት። ይህም በዓለም አቀፍ እና በአገር ውስጥ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ከፍተኛ ትችት እንዲሰነዘርባት ምክንያት ሆኗል።