ዴሞክራቶች ለአሜሪካ ጦር ያስተላለፉት መልዕክት "ዓመፅ የተሞላበት እና በሞት የሚያስቀጣ ነው" ሲሉ ትራምፕ ገለጹ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ስድስት የዴሞክራት ሕግ አውጪዎች የአሜሪካ ጦር አባላት ሕገ ወጥ ትዕዛዞችን እንዲቃወሙ የሚያሳስብ ቪዲዮ ከለቀቁ በኋላ "በዓመፅ የተሞላ እና በሞት የሚያስቀጣ ባህሪ" ሲሉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሱ።

"ይህ በጣም መጥፎ፤ ለአገራችንም አደገኛ ነው። ንግግራቸውን መታገስ አይገባንም። ዓመፅ የተሞላበት የከሃዲዎች ባህሪ!!! እሰሯቸው???" ሲሉ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጽፈዋል።

በወታደራዊ ወይም በስለላ ተቋም ውስጥ ያገለገሉት ስድስቱ ሕግ አውጪዎች የትራምፕን አስተያየት አደገኛ ከማለት ባለፈ በሕዝብ በተመረጡ ባለሥልጣናት ላይ የተፈጸመ ዛቻ እንደሆነ ተናግረዋል።

"ምንም ዓይነት ማስፈራሪያ ወይም የዓመፅ ጥሪ ከዚያ ኃላፊነት አያግደንም" ሲሉ በጋራ መግለጫቸው ገልጸዋል።

በዴሞክራቶች የተዘጋጀው ቪዲዮ በሚቺጋን ሴናተር ኤሊሳ ስሎትኪን የተጋራ ሲሆን፤ የአሪዞናው ሴናተር ማርክ ኬሊ፤ የፔንስልቬንያው ክሪስ ዴሉዚዮ፤ የኒው ሃምፕሻየሯ ማጊ ጉድላንደር፣ የፔንስልቬንያዋ ክሪስሲ ሁላሃን እና የኮሎራዶውን ጄሰን ክሮውን ያካተተ ነው።

በባሕር ኃይል ውስጥ ያገለገሉት እና የቀድሞ የጠፈር ተመራማሪ ሴናተር ኬሊ "ሕጎቻችን ግልጽ ናቸው። ሕገ ወጥ ትዕዛዞችን መቃወም ይፈቅዳሉ" ብለዋል።

"ሕግን ወይም ሕገ መንግሥታችንን የሚጥሱ ትዕዛዞችን ማንም መፈጸም የለበትም" ሲሉ የሕግ አውጪዎቹ በቪዲዮው ላይ ተናግረዋል።

"ይህ አስተዳደር ዩኒፎርም የለበሱ የጦር እና የስለላ ባለሙያዎቻችንን ከአሜሪካ ዜጎች ጋር እያጋጨ ነው። እንደኛ ሁሉ ሁላችሁም ይህንን ሕገ መንግሥት ለመጠበቅ እና ለመከላከል ቃለ መሃላ ፈጽማችኋል። በአሁኑ ጊዜ በሕገ መንግሥታችን ላይ የሚነሱት ስጋቶች ከውጭ የመጡ ብቻ ሳይሆኑ ከውስጥ የመጡ ጭምር ናቸው" ብለዋል።

ትራምፕ ሐሙስ ጠዋት በትሩዝ ሶሻል ላይ ምላሽ የሰጡት ተከታታይ ጽሑፎች በማቅረብ ነው።

"ይህ ከፍተኛ የዓመፅ ባህሪ ይባላል። እነዚህ የአገራችን ከዳተኞች ተይዘው ለፍርድ መቅረብ አለባቸው። ቃላቸው እንዲሰማ ሊፈቀድ አይገባም። ከእንግዲህ አገር አይኖረንም!!! ምሳሌ መሆን አለበት" ሲሉ ሐሙስ ዕለት ጽፈዋል።

ቀጥለውም "ይህ በጣም መጥፎ እና ለአገራችንም አደገኛ ነው። ቃላቶቻቸው እንዲሰማ ሊፈቀድላቸው አይገባም። የከሃዲዎች የዓመፅ ባህሪ ነው!!! እሰሯቸው???" ብለዋል።

በሦስተኛው ጽሑፋቸው ደግሞ "በሞት የሚያስቀጣ የዓመፅ ባህሪ!" ሲል ጽፈዋል።

የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ካሮሊን ሊቪት፤ ትራምፕ የኮንግረስ አባላት እንዲገደሉ ጥሪ አቅርበዋል የሚለውን አስተያየት ሐሙስ ዕለት ውድቅ አድርገዋል።

"እዚህ ያላችሁ ብዙዎቻችሁ ስለ ፕሬዚዳንቱ ምላሽ ማውራት ትፈልጋላችሁ። ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ በዚህ መንገድ ምላሽ እንዲሰጡ ያደረጋቸው ነገር አይደለም" ከማለት ባለፈ የሕግ አውጭዎቹ ጦሩ "ሕጋዊ ትዕዛዞችን" እንዲቃወሙ አበረታተዋል በማለት ከሰዋል።

በአሜሪካ የፖለቲካ ንግግር ላይ የተጨመረው ስጋት

ሊቪት ሐሙስ ከሰዓት በኋላ በዋይት ሃውስ በተደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ትራምፕ የኮንግረስ አባላትን "መግደል" ይፈልጉ እንደሆነ ሲጠየቁ "በጭራሽ" ሲሉ በፍጥነት መልሰው፤ መገናኛ ብዙኃን በሕገ ወጡ አባላት አስተያየት ላይ ማተኮር አለባቸው ብለዋል።

"ለ1.3 ሚሊዮን የጦር አባላት የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ እንዲቃወሙ እንጂ ሕጋዊ ትዕዛዞችን እንዳይከተሉ ቃል በቃል እየነገሩ ነው" ሲሉ ሊቪት ሐሙስ ዕለት በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተናግሯል።

"ምናልባትም በሕግ የሚያስቀጣ ሊሆን ይችላል" በማለት አክለዋል።

በአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ያሉ አመራሮች፤ ከካፒቶል ፖሊስ ጋር በመተባበር ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የሕግ አውጭዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን በበቂ ሁኔታ ለመጠበቅ እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የዴሞክራቲክ ምክር ቤት አባል ሃኪም ጄፍሪስ የትራምፕን ንግግር ነቅፈው፣ ፕሬዚዳንቱ "አንድ ሰው ከመገደሉ በፊት የዓመፅ ንግግራቸውን ማንሳት አለባቸው" ብለዋል።

ሪፐብሊካኑ የምክር ቤት አፈ ጉባኤ ማይክ ጆንሰን ግን ትራምፕ የዴሞክራቶችን ቪዲዮ "እጅግ ተገቢ ያልሆነ" እና "በጣም አደገኛ" ሲሉ ጠርተውታል በማለት ፕሬዝዳንቱን ተከላክለዋል።

ፍትሕ ሚኒስቴር እና ፔንታጎን ጉዳዩን ይገመግማሉ ብለዋል።

የትራምፕ አስተያየት የመጣው በአሜሪካ በፖለቲካዊ ምክንያት የሚደርሱ ጥቃቶች ዙሪያ ከፍተኛ ስጋት ባንዣበበት ወቅት ነው።

በጥቅምት ወር በፒው የምርምር ማዕከል የተደረገ ጥናት 85 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት እየጨመረ መሆኑን ያምናሉ። ፖለቲኮ እና ፐብሊክ ፈርስት በኅዳር ወር ያወጡት የሕዝብ አስተያየትም ይህንኑ ደግፏል።

ትራምፕም ጭምር በሁለት የግድያ ሙከራዎች ኢላማ ተደርገዋል። አንደኛው ባለፈው ዓመት በፕሬዝዳንታዊ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሲሆን አንድ ሰው ተገድሏል። ትራምፕን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሰዎች ቆስለዋል።

በዚህ ዓመት ብቻ በርካታ ትላልቅ ክስተቶች አጋጥመዋል። የወግ አጥባቂ የፖለቲካ ተንታኝ ቻርሊ ከርክ ግድያ እና በዴሞክራቷ የፔንስልቬንያ ገዥ ጆሽ ሻፒሮ ቤት ላይ የተፈጸመው የእሳት ቃጠሎ እና የዴሞክራቷ የሚኒሶታ የሕግ አውጭ እና ባለቤቷ ግድያ ተጠቃሽ ናቸው።