የቀድሞ ፍቅረኛውን ሲደበድብ በቪዲዮ የታየው ታዋቂው ራፐር ዲዲ ይቅርታ ጠየቀ

ኬሲ እና ዲዲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የቀድሞ ፍቅረኛው ካሳንድራ ቬንቹራን ሲደበድባት እና ሲገፈትራት በበሲሲቲቪ ካሜራ የታየው ሾን ኮምቢስ ለድርጊቱ ይቅርታ ጠይቋል።

በመድረኩ ስሙ ዲዲ እየተባለ የሚጠራው ራፐሩ የቀድሞ ፍቅረኛው የሆነችው ዘፋኟ ኬሲን በ2016 ሆቴል ውስጥ ሲደበድባት የሚያሳይ ቪድዮ ተለቋል።

በኢንስታግራም ገፁ በለቀቀው ቪዲዮ "ይቅርታ ለማይገባው" ድርጊቱ ሙሉ ኃላፊነት እንደሚወስድ ተናግሯል።

በሆቴሉ የደኅንነት ካሜራ [ሲሲቲቪ] የተቀረፀውን ቪዲዮ ለሕዝብ ይፋ ያደረገው የአሜሪካው ሲኤንኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው።

"ባደረግኩት ጊዜ እጅግ ፀፅቶኝ ነበር። አሁንም በጣም ተፀፅቻለሁ" ይላል ዲዲ በመግለጫው።

"በወቅቱ ፕሮፌሽናል የሆነ ሰው እንዲረዳኝ ሞክሬ ነበር። የሥነ-ልቡና ባለሙያ ምክር ወስጃለሁ። ፈጣሪዬንም ይቅርታ እና ሞገስ መልሶ እንዲያላብሰኝ ጠይቄዋለሁ። በጣም ይቅርታ።"

ራፐሩ አክሎ "በየጊዜው የተሻለ ሰው ለመሆን ቁርጠኛ ነኝ" ብሏል።

ነገር ግን በሙዚቃ፣ ሞዴሊንግ እና ትወና ሥራዋ የምትታወቀው ኬሲ ጠበቃዎች የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ በሰጡት ቃል የዲዲ ይቅርታ "ስለጎዳቸው ሰዎች ሳይሆን ስለራሱ ብቻ ያወራበት ነው" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ኬሲ እና ሌሎች በርካታ ሴቶች የደረሰባቸውን ስቃይ ወጥተው ሲናገሩ ድርጊቱን ክዶ ነበር።እንዲያውም ተበዳዮቹ ገንዘብ ፈልገው ነው የሚል አስተያየት ሲሰጥ ነበር" ትላለች ጠበቃ ሜሬዲት ፊርቶግ።

"በተደጋጋሚ የካደው ነገር እውነት ሆኖ ሲገኝ ጊዜ ነው ይቅርታ ለመጠየቅ የተገደደው። ይህ ደግሞ ምን ያክል እንደተጋለጠ ያሳያል። ተአማኒ ባልሆኑ ቃላቶቹ ማንም አይገዛም።"

ምንም እንኳ ቢቢሲ ቪዲዮውን መርምሮ ባያጣራም ድርጊቱ በአውሮፓውያኑ መጋቢት 5/2016 እንደተፈፀመ ይጠቁማል።

ሲኤንኤን የለቀቀው ቪዲዮ ሾን ኮምብስ በወቅቱ ፍቅረኛው የነበረችው ካሳንድራን ወደ መሬት ገፍትሮ ከጣላት በኋላ በወደቀችበት ሲመታት ያሳያል። ቀጥሎ ደግሞ ካናቴራዋን ይዞ ሊጎትታት ሲሞክራና አንዳች ቁስ ሲወረውርባት ያስመለክታል።

ሲኤንኤን እንደሚለው ቪድዮው የተቀረፀው አሁን በተዘጋው ሎስ አንጀለስ በሚገኘው ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ነው።

ዲዲ ይቅርታ ቢጠይቅም እስካሁን ስለ ቪዲዮው ያለው ነገር የለም።

የካሳንድራ ጠበቃዎች ከዚህ ቀደም በለቀቁት መግለጫ "ለማየት የሚከብደው ቪዲዮ የኮምብስን አስጠያፊና አስከፊ ባሕሪ የበለጠ የሚያሳይ ነው" ብለዋል።

የሎስ አንጀለስ ግዛት አቃቤ ሕግ ቢሮ አርብ ዕለት በለቀቀው መግለጫ ቪዲዮውን ተመርኩዞ ክስ ለመመሥረት ጊዜው ሳይረፍድ አይቀርም ብሏል።

ጥንዶቹ ግንኙነት የጀመሩት ካሳንድራ የ19 ዓመት ወጣት ዲዲ ደግሞ የ37 ዓመት ግለሰብ ሳለ ነው።

ባለፈው ኅዳር ካሳንድራ በመድፈር እና የወሲብ ንግድ በመፈፀም ዲዲን ከሳው ጉዳዩ ከፍርድ ቤት ውጭ በድርድር ችሎት እንዲጠናቀቅ ተደርጓል።

የዲዲ ጠበቃ ቤንጃሚን ብራፍማን በወቅቱ የድርድር ችሎቱ ውጤት ማለት "ደንበኛዬ በፍፁም ድርጊቱን አምኗል ማለት አይደለም" ብለው ነበር።

ከዚህ ጊዜ በኋላ በርካታ ሴቶች ራፐሩ ወሲባዊ ጥቃት እና አካላዊ ጉዳት አድርሶብናል ሲል ክስ መሥርተዋል።

ባለፈው ወር ሎስ አንጀለስና ማያሚ የሚገኙ የራፐሩ ልጥጥ መኖሪያ ቤቶች በፌዴራል የምርመራ ቡድን አባላት ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎባቸዋል።