ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጣሊያን ግዙፉን የጎማ ፋብሪካ በቻይና መንግሥት ለተያዘ ኩባንያ አልሸጥም አለች
በቻይና መንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደረው ፒሬሊ የተባለውን ግዙፉን የጎማ አምራች ኩባንያ እንዳይገዛ ጣሊያን አግዳለች።
የጣሊያን መንግሥት የፒሬሊን ገለልተኝነት ለመጠበቅ የወሰድኩት እርምጃ ነው ብሏል።
በቻይና መንግሥት የሚመራው ሲኖኬም የተሰኘው የኬሚካል ኩባንያ የፒሬሊ ጎማ ትልቁ ባለድርሻ ነው።
151 ዓመት የሞላው መቀመጫው ሚላን የሆነው የጎማ ኩባንያ 37 በመቶ ድርሻው በቻይናው ድርጅት የተያዘ ነው።
ቤይዢንግ እና ምዕራባዊያን ሃገራት ውጥረት ውስጥ ናቸው። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደግሞ ይህን ለማብረድ ወደ ቻይና አቅንተዋል።
እሑድ ዕለት ፒሬሊ ባወጣው መግለጫ፤ የጣሊያን መንግሥት የፒሬሊ አለቃ ማርኮ ፕሮቬራ ንብረት የሆነው ካምፊን የተሰኘው ድርጅት ብቻ ነው ዋን ሥራ አስኪያጅ መምረጥ የሚችለው የሚል መመሪያ ማውጣቱን ይፋ አድርጓል።
መግለጫ አክሎ ፒሬሊ ምንም ዓይነት የሥልጣን ለውጥ ሲያደርግ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ የመመርመር ኃላፊነት አለበት ይላል።
ባለፈው መጋቢት የቻይናው ኩባንያ በድርጅቱ ያለውን ድርሻ ማሻሻል እንደሚፈልግ ለጣሊያን መንግሥት ገልጦ ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ መንግሥት ለሃገሪቱ ትልቅ ጥቅም አላቸው የሚላቸውን ድርጅቶች የሚጠብቅበት ማዕቀፍ አለው።
በፈረንጆቹ 2015 ፒሬሊ 7.1 ቢሊዮን ዩሮ በሆነ ዋጋ ለቻይናው ኬምቻይና እና ለካምፊን ተሽጦ ነበር።
ከስድስት ዓመታት በኋላ ኬምቻይና የቻይና ንብረት ከሆነው ሲኖኬም ጋር ጥምረት ፈጠረ።
ከሁለቱ ድርጅቶች ባሻገር ሌላኛው የቻይና መንግሥት ንብረት የሆነው ሲልክ ሮድ ኢንቨስትመንት ፈንድ 9 በመቶ የፒሬሊ ድርሻ አለው።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊከን ቤይዢንግ ያላቸውን ቆይታ እያጠናቀቁ ነው።
አንድ የዋሺንግተን ከፍተኛ ባለሥልጣን በቻይና ጉብኝት ሲያደርግ ከረዥም ጊዜ በኋላ ነው።
በንግድ፣ ታይዋንና ደኅንነት ጉዳይ ቻይና ከምዕራባዊያን ሃገራት ጋር ያላት ግንኙነት እየሻከረ መጥቷል።
ሁለቱ ኃያላን የዓለም ምጣኔ ሃብት አንቀሳቃሾች ቻይና እና አሜሪካ የከረረውን ግንኙታቸውን ያለዝቡ ይሆን የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።