የትራምፕን የግድያ ሙከራ ተከትሎ የሴክሬት ሰርቪስ ኃላፊ ሥልጣናቸውን ለቀቁ

የሰክሬት ሰርቪስ ዳይሬክተር ኪምበርሊ ቺትል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የዶናልድ ትራምፕን የግድያ ሙከራ ተከትሎ ፕሬዝዳንቱን በዋነኝነት መጠበቅ ሥራው የሆነው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ጥበቃ ቡድን (ሴክሬት ሰርቪስ) ዳይሬክተር ኪምበርሊ ቺትል ሥራቸውን ለቀቁ።

“የግድያ ሙከራ እንዲፈጠር ለፈቀደው ክፍተት ኃላፊነቱን እወስዳለሁ” ያሉት ኪምበርሊ፤ “ሁልጊዜም ቅድሚያ የምሰጠው ለኤጀንሲው ነው” ካሉ በኋላ ሥራ የመልቀቅ ውሳኔ ቀላል እንዳልነበር ገልጸዋል።

ኪምበርሊ የሚመሩት ኤጀንሲ ሥራውን መከወን አልቻለም በሚል የዴሞክራቲክ እና የሪፐብሊካን ሕግ አውጪዎች ስልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው እንዲለቁ ሲጠይቋቸው ነበር።

ጥያቄው የቀረበው ሰኞ ዕለት ውጥረት በበዛበት የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ በፔንሲልቬንያ ግዛት በትራምፕ ላይ በተቃጣው የመግደል ሙከራ ዙሪያ የተቋሙን የደኅንነት ዝግጅት በተመለከተ ጥያቄ በቀረበበት ወቅት ነው።

በተኩሱ የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ጨምሮ ሦስት ሰዎች ቆስለዋል።

የሰኞው ስብሰባ ለኪምበርሊ ቺትል በጣም ከባድ ነበር ተብሏል።

ሕግ አውጪዎቹ በኃላፊዋ መልስ እና በተቋሙ የመረጃ እጦት ሲሳለቁ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያየ አቋም የሚያሳዩት ሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ የቆሙበት አጋጣሚ ነበር ተብሏል።

ለስድስት ሰዓታት ለሚጠጋ ጊዜ የምክር ቤት አባላቱ ስለጥቃቱ፣ ተጠርጣሪው ቶማስ ማቲው ክሩክስ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ጣሪያ ላይ እንዴት እንደ ወጣ እና ተጠርጣሪ መኖሩ ከተነገረ በኋላ ለምን ትራምፕ መድረኩ ላይ እንዲወጡ ተፈቀደ የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበዋል።

ከስብሰባው በኋላ የኮሚቴው የሪፐብሊካን እና ዲሞክራቲክ ፓርቲዎች መሪ የሆኑት ጄምስ ኮሜር እና ጄሚ ራስኪን ኃላፊዋ ከሥራቸው መልቀቅ እንዳለባቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ ልከዋል።

“በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሂደት ወቅት ኮሚቴው እና የአሜሪካ ሕዝብ እርስዎ የማይሰጧቸውን ከባድ ተቋማዊ ተጠያቂነት እና ግልጽነት ይጠይቃሉ” ይላል ደብዳቤው።

“አዲሱ አመራር ይህንን ችግር በፍጥነት እንዲፈታ እና የሚመለከተውን ኮንግረስ እና የአሜሪካን ሕዝብ አመኔታ እንዲገነባ ለማስቻል የመጀመሪያው እርምጃ ከዳይሬክተርነት እንዲለቁ እንጠይቃለን” ሲልም አክሏል።

ቼትል በስብሰባው ወቅት ለደኅንነት ችግሮች ኃላፊነቱን ወስደው የፔንሲልቬኒያው ክስተት “በአገልግሎቱ የአስርት ዓመታት ሥራ ውስጥ ከታየው እጅግ በጣም ከፍተኛው ውድቀት” መሆኑን ያመኑ ሲሆን፣ ይህም ብዙ የሕግ አውጪዎችን አበሳጭቷል።

ሥራቸውን ለመልቀቅ የቀረቡትን ጥሪዎች ወደ ጎን በማለት “በአሁኑ ጊዜ አገልግሎቱን ለመምራት ምርጧ ሰው” መሆናቸውን አስታውቀዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዳይሬክተሯ እየተካሄደ ያለውን ምርመራ በመጥቀስ ጥቂት ጥያቄዎችን በቀጥታ መልሰዋል።

የኮሚቴው ሊቀመንበር ኮመር “የአሜሪካ ሕዝብ ጥያቄዎች አሉት። ምላሽም ይገባዋል” ብለዋል።

“መልስ እንድትሰጡ ቢፈለግም እመቤቴ ይህንን አላደረጉም።”

ውጥረት የበዛበት በዚህ ስብሰባ ላይ ወደ ቁጣ የሚቀየር የሚመስልበት አጋጣሚም ተፈጥሯል። የሕግ አውጪዎች ምስክር ላይ ጮኸዋል፤ የዳይሬክተሩን ታማኝነት እና ብቃት ጥያቄ አንስተውበታል።

የፍሎሪዳ ኮንግረስ አባል አና ፓውሊና ሉና “በእርስዎ አፈጻጸም ተሳቅቄያለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

የቺትል መልሶች የኮሚቴውን የሕግ አውጪዎች ቁጣ የቀሰቀሱ ይመስላሉ። ብዙዎቹም ሥራ ለመልቀቅ እምቢ ማለታቸውን ከቀጠሉ መባረር አለባቸው ብለዋል።

የትራምፕ አጋር የሆኑት የኦሃዮ ሪፐብሊካን ጂም ጆርዳን “አንዳንድ መሠረታዊ ጥያቄዎችን የሚመልሱ አይመስልም። በፕላኔቷ ላይ በጣም ታዋቂ ከሆኑት ግለሰቦች አንዱን ለመጠበቅ የማይረባ አካሄድ የሚመርጡ ይመስላል” ብለዋል።

ቺትል የሚያደርጉት መክፈቻ ንግግር እንዴት መገናኛ ብዙኃን እጅ ገባ በሚለው ዙሪያ በተደረገው አስጨናቂ ውይይት ወቅት የሳውዝ ካሮላይና ሪፐብሊካን ናንሲ ማሴ “ታማኝ እየሆኑ አይደለም ወይም እየዋሹ ነው። ዝም ብለው ይሸሻሉ!” ብለዋል። በኋላም ቺትልን ከሥራ ማባረር እንዲቻል ለኮንግረሱ ጥያቄ አቀርበዋል።

የጆርጂያ ሪፐብሊካን ማርዮሪ ቴይለር ግሪን ደግሞ ቺትልን “ሙሉ ለሙሉ ወድቀዋል” በማለት ጮኸው ተናግረዋል።

ግሪን “መላው ሕዝብ ሥልጣን እንዲለቁ እየጠየቀ ነው” ሲሉ አክለዋል።

ቼትል እስካሁን ድረስ ከፔንሲልቬኒያው ክስተት ጋር በተያያዘ በየትኛውም የአገልግሎቱ ኃላፊዎች ወይም ሠራተኞችላይ ቅጣት እንዳልተጣለባቸው አምነዋል።

እንደ ቺትል ገለጻ ስለ ጥቃቱ የመጀመሪያ የምርመራ ውጤት በሚቀጥሉት 60 ቀናት ውስጥ ይፋ ይሆናል። በዚህ የጊዜ ሰሌዳም የኮሚቴ አባላቱ አፊዘውበታል።

ጀምስ ኮመር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኒውዮርኩ ዴሞክራት አሌክሳንድሪያ ኦካሲዮ-ኮርቴዝ በበኩላቸው በውጥረት በተሞላ የምርጫ ወቅት የምርመራ ውጤቱ መዘግየት ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

“ይህ ቲያትር አይደለም። ይህ ስለ ቀልድ አይደለም። ይህ በዓለም አቀፍ እና በአገር ውስጥ በጣም ትኩረት ከሚሰጣቸው የአንዱ ግለሰብ ደኅንነት ጉዳይ ነው። መልስ ሊኖር ይገባል። የፖሊሲ ውሳኔዎችን ማድረግ አለብን” ብለዋል።

“ካልሆነ በጨለማ እየተጓዝን ነው” ሲሉም አክለዋል።

የቼትል የወደፊት ዕጣ ፈንታን በተመለከተ አንጻራዊ አንድነት ቢታይም በሪፐብሊካኖች እና በዴሞክራቶች መካከል አንዳንድ አለመግባባቶችም ነበሩ።

በርካታ ሪፐብሊካኖች በትራምፕ የደኅንነት ጥበቃ ውስጥ የተመደቡ እና ከቅጥራቸው ጋር በተያያዘ ሴት የሴክሬት ሰርቪስ ጠባቂዎችን ብቃት ጥያቄ አንስተውበታል።

እንደ የኮሎራዶው ላውረን ቦበርት እና የፍሎሪዳዋ ሉና ያሉት ደግሞ በበይነ መረብ ላይ የሚዘዋወሩ የሴራ ትንታኔዎችን አንስተዋል።

የፍሎሪዳ ሪፐብሊካን ሚካኤል ዋልትዝ ለተፈጠረው አሉባልታ ቺትልን ወቅሰው፤ መረጃ በሌለበት ሁኔታ የተሳሳተ መረጃ “አየሩን ይቆጣጠራል” በማለት ተከራክረዋል።

የበትለሩን የተኩስ ልውውጥን የተመለከቱ በርካታ የዐይን እማኞች ቺትል በሰጡት መልስ ብስጭት እንዲሰማቸው ማድረጉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።