ትችት ጽፎብኛል ያለውን ጋዜጠኛ የገደለው አሜሪካዊ ፖለቲከኛ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በስልጣን ላይ ባለበት ወቅት ትችቶችን ጽፎብኛል ያለውን ጋዜጠኛ የገደለው የአሜሪካ ኔቫዳ ግዛት ፖለቲከኛ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት።
የ47 ዓመቱ ፖለቲከኛ ሮበርት ቴልስ የላስ ቬጋስ ሪቪው ጆርናል የምርመራ ጋዜጠኛ የሆነውን ጄፍ ጀርማንን በመግደል ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።
ፖለቲከኛው ጋዜጠኛውን በስለት ወግቶ በመግደል በቁጥጥር ስር የዋለው ከሁለት ዓመታት በፊት ነው።
በችሎቱ ወቅት አቃብያነ ህግ በጋዜጠኛው የጣት ጥፍሮች ስር የተገኙትን የፖለቲከኛውን ዘረ መል (ዲኤንኤ) ማስረጃዎች አቅርበዋል።
ፖለቲከኛው በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ አይደለሁም ብሏል።
ለሁለት ቀናት ያህል ከፈጀው ችሎት በኋላ ረቡዕ፣ ነሐሴ 22/ 2016 ዓ.ም የጥፋተኝነት ብያኔ ተላልፏል።
ክላርክ በተሰኘው ግዛት የህዝብ አስተዳዳሪነት በአውሮፓውያኑ 2018 ተመርጦ የነበረው ሮበርት ቴልስ ብያኔው በሚተላለፍበት ወቅት ፊቱ ላይ ስሜት በማይነበብበት ሁኔታ ተቀምጦ ነበር።
ችሎቱ ጥፋተኛ ነው የሚል ውሳኔ ሲያሰማ ፖለቲከኛው አንገቱን ድፍት ሲያደርግ ታይቷል።
ፖለቲከኛው ሆን ብሎ፣ በታሰበበት እና በታቀደበት መንገድ ጋዜጠኛውን መግደሉን ፍርድ ቤቱ አረጋግጧል ብሏል።
የዕድሜ ልክ እስራት የተበየነበት ፖለቲከኛ ከ20 ዓመታት እስር በኋላ ይግባኝ መጠየቅ ይችላል።
ችሎቱ ለሁለት ቀናት ከተወያየ በኋላ ብያኔ የተላለፈ ሲሆን አጠቃላይ የፍርድ ሂደቱ ሁለት ሳምንታትን ፈጅቷል።
በርካታ የወንጀል መርማሪዎችን ጨምሮ፣ ፖለቲከኛውን የሚያውቁት ግለሰቦች፣ ፖለቲከኛው እና በርካታ ምስክሮች እንዲሁም የምርመራ ውጤቶች ለፍርድ ቤቱ ቀርበዋል።
ክሱን የካደው እና ንጹህ ነኝ ሲል የተከራከረው ፖለቲከኛ ወንጀሉ ሆን ብሎ እሱን ለማጥመድ የተቀነባበረ ነው ብሏል።
የ69 ዓመቱ ጋዜጠኛ በአንገቱ እና ሆዱ አካባቢ በስለት ተወግቶ የተገደለው ኔቫዳ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር።
ፖለቲከኛው በስልጣን በነበረበት ወቅት ከአንድ ሰራተኛው ጋር “ያልተገባ ግንኙነት” መመስረትን ጨምሮ ሌሎች ትችቶችን የሚያሳዩ ጽሁፎችን ጋዜጠኛው እንደጻፈ አቃብያነ ህግ ተናግረዋል።
የላስቬጋስ ሪቪው ጆርናል ዘገባን ተከትሎ ፖለቲከኛው ለሁለተኛ ጊዜ በሚያደርገው የህዝብ አስተዳዳሪነት ምርጫ ተሸንፏል።
ፖሊስ ያገኘው ቪዲዮ ጋዜጠኛውን የገደለው ግለሰብ ትልቅ ኮፍያ አጥልቆ በጋዜጠኛው ቤት አካባቢ ሲያንዣብብ አሳይቷል።ባለስልጣናቱ የጋዜጠኛው የተቆራረጡ የተወሰኑ አካላት በፐለቲከኛው ቤት መገኘቱን ተናግረዋል።
የፖለቲከኛው ጠበቆች በበኩላቸው በደንበኛው ቤት ውስጥ የተገኙ ማስረጃዎች ሆን ተብለው የተቀነባበሩ ናቸው ሲሉ ተከራክረዋል።
አንጋፋው ጋዜጠኛ ጄፍ ጃርማን ለአራት አስርት ዓመታት ያህል የኔቫዳን ከተማ እና ሙስናዎችን ያጋለጡ ዘገባዎችን ሰርቷል። ጋዜጠኛው በሞተበት ወቅት ስለ ፖለቲከኛው አንድ ጽሁፍ ሊያሳትም እንደነበር ተገልጿል።












