የባርሴሎና ክለብ ዳኝነትን ‘በገንዘብ ገዝቷል’ የሚል የሙስና ክስ ቀረበበት

ጆን ላፖርታ የባርሴሎና ክለብ ፕሬዝዳንት

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ጆን ላፖርታ የባርሴሎና ክለብ ፕሬዝዳንት
ታትሟል

ታላቁ የስፔን እግር ኳስ ክለብ ባርሳ ዳኝነትን በጉቦ ሲገዛ ነው የኖረው በሚል ክስ ቀረበበት።

ክለቡ ክሱን አስተባብሏል።

ክሱ እንደሚለው ባርሴሎና ከፍተኛ ገንዘብ “ዳዝኒል-95” ለተባለ ኩባንያ ሲከፍል ነበር።

ይህ ኩባንያ በባለቤትነት የተያዘው ደግሞ ሆዜ ማሪያ ኤንሪካዝ ኔግሬራ በሚባሉ ግለሰብ ነው።

እኒህ ግለሰብ ደግሞ የእግር ኳስ ዳኛ፣ እንዲሁም የቀድሞው የስፔን የእግር ኳስ ዳኞች ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የነበሩ ሰው ናቸው።

ክሱን የመሠረተው የባርሴሎና ከተማ ዐቃቢ ሕግ ነው።

ጉዳዩን ለመጀመርያ ጊዜ ካዴና ሴር የሚባል የሬዲዮ ጣቢያ ነው ይፋ ያደረገው።

ጣቢያው ባርሳ ለኚህ ሰው ከፍተኛ ገንዘብ ሲከፍል እንደኖረ በምርመራ ጋዜጠኝነት ይፋ ካደረገ በኋላ ነው በክለቡ ምርመራው የተጀመረው።

ጣቢያው እንዳለው ሚስተር ኔግሬራና ኩባንያቸው “ዳዝኒል-95”፣ ከ2001-2018 ዓ/ም ከባርሴሎና ክለብ ምክንያቱ በውል ያልታወቀ ገንዘብ ሲከፈላቸው ነበር።

በነዚህ ዓመታት ባርሴሎና ክለብ ለዚህ ዳዝኒል-95 ለሚባል ኩባንያ በድምሩ ከስምንት ሚሊዮን ዩሮ በላይ ከፍሏል ይላል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትናንት ዐርብ የባርሴሎና ፍርድ ቤት ባስቻለው ችሎት ክለቡና ሚስተር ኔግሬራ እምነት በማጉደል እና በሙስና ክስ ቀርቦባቸዋል።

በባርሴሎና ከተማ ዐቃቢ ሕግ የቀረበው ይህ ክስ ከእግር ኳስ ባርሳ ሌላ ፕሬዝዳንቱን ጆሴፕ ማሪያ ባርቶሜን እና ሳንድሮ ሮሴልን አካቷል።

ዐቃቤ ሕግ እንዳለው ባርሴሎና ክለብና ግለሰቡ ኔግሬራ በቃል ባደረጉት ስምምነት ለዚህ በሚሊዮን ለሚቆጠር የእጅ መንሻ ክፍያ በምላሹ ኔግሬራ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው በዳኝነት ለባርሳ የሚያደላ ውሳኔዎችን በቻሉት አቅም እንዲወስኑ ተስማምተዋል።

የላ ሊጋ አለቃ የሆኑት ዣቪየር ቴባስ ባለፈው ወር የአሁኑ የክለቡ ፕሬዝዳንት ጆን ላፖርታ ይህን ክፍያ የተመለከተ ማብራሪያ መስጠት ካልቻሉ ሥልጣናቸውን ዛሬ ነገ ሳይሉ ሊለቁ ይገባል ሲል ነበር።

ላፖርታ በበኩላቸው ለዣቪየር ቴባስ ፍላጎት ብዬ ሥልጣኔን አለቅም፤ ክለባችን ዳኝነትን በገንዘብ አልገዛም፤ የሚወራው ሁሉ ቅጥፈት ነው ሲሉ ተከላክለዋል።

ይህ ያልተገባ ክፍያ መፈጸሙ ተደረሰበት የተባለው ዳዝኒል-95 ኩባንያ ዓመታዊ ግብር ምርመራ በተደረገበት ሰዓት ነው።

ባርሴሎና ክለብ ይህን ከፍተኛ ገንዘብ ለኩባንያው መክፈሉን አምኖ ነገር ግን “እንዲያማክሩኝ ነው ገንዘብ የከፈልኩት” ብሏል።

አሁን በስፔን ላ ሊጋ ከሚሳተፉት 20 ክለቦች 18ቱ በባርሴሎና ላይ የቀረበው ክስ እንዳሳሰባቸውና የራሳቸውን ምርመራና እርምጃም እንደሚወስዱ ገልጠዋል።

ስምንት ጊዜ ከክለቡ ጋር ዋንጫ ማንሳት የቻለው የባርሴሎና አሰልጣኝ ዣቪ በበኩሉ ስለጉዳዩ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ተናግሯል።

“ሁሌም ማሸነፍን እሻለሁ። ነገር ግን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ብቻ፤ እያጭበረበርን ከነበረማ ወደቤት ብሄድ እመርጥ ነበር” ብሏል።

ይህን አስተያየቱን የሰጠው ባርሳ ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር በአውሮፓ ሊግ 2 አቻ ከተለያየ በኋላ ነው።