ሱቶን፡ በሊጉ ሊቨርፑል እና አርሰናል ድል ያደርጋሉ፤ ዩናይትድም ከታሪካዊ ሽንፈቱ ያገግማል

ጋክፖ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ባለፈው ሳምንት በፕሪሚየር ሊጉ ተአምር ያስባሉ ውጤቶች ተዝግበዋል።

ዩናትድ በሊቨርፑል 7 ለ 0 የተረመረመበት፤ መድፈኞቹ 2 ለ 0 ከመመራት ተነስተው 90+7 ደቂቃ ላይ የማሸነፊያ ጎል ያስቆጠሩት በ26ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ነበር።

27ኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችም ቅዳሜ ጀምረው እስከ ቀጣይ ሳምንት አጋማሽ ቀጥለው ይካሄዳሉ።

የቢቢሲ የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱቶን የጨዋታ ግምቶቹን እንደሚከተለው አስቀምጧል።

ቅዳሜ

በርንማውዝ ከ ሊቨርፑል

በርንመዝ ከ ሊቨርፑል

ሊቨርፑል ባለፈው ሳምንት ማንችስተር ዩናይትድን ሰባት ለምንም ባሸነፈበት ጨዋታ ያለውን የፊት መስመር ጥንካሬውን አሳይቷል። የተከላካይ መስመሩም ድንቅ ነበር።

“ሊቨርፑል በሊጉ ተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ጎል አለማስተናገዱ ግርምት ፈጥሮብኛል” ይላል የቢቢሲው እግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱቶን።

አሁን ዋናው ጥያቄ ዩናይትድን በሰፊ የጎል ልዩነት ያሸነፈው የክሎፕ ቡድን ወደ ቀድሞ ብቃቱ ተመልሷል ወይ የሚለው ነው?

ዕድል ፈንታቸውን በመቀየር እስከ አራት ባለው ደረጃ ይጨርሳሉ?

ይሄን ጊዜ የሚፈታው ይሆናል።

ከዚህ ጨዋታ በኋላ ሊቨርፑል ማንችስትር ሲቲ፣ ቼልሲ እና አርስናልን በአራት ሳምንታት ውስጥ ይገጥማል። ከእነዚህ ጨዋታዎች በፊት በቅዳሜው ጨዋታ ነጥብ መጣል የለባቸውም።

ከዩናይትድ ጋር በሁለተኛው አጋማሽ የነበራቸውን ጨዋታ ከደገሙ ያሸንፋሉ። ብዙ ጎሎችን ማስቆጠራቸውን ግን እጠራጠራለሁ።

ግምት፡ በርንመዝ 0 - 2 ሊቨርፑል

ቀይ መስመር

ኤቨርተን ከ ብሬንትፈርድ

ይህ ለመገመት አስቸጋሪ ጨዋታ ነው።

ባለፈው ሳምንት ኤቨርተን ዕድለ ቢስ በመሆኑ ኖቲንግሃም ፎረስትን ማሸነፍ አልቻለም።

ብሬንትፈርድ ደግሞ ባለፉት 12 የሊግ ጨዋታዎች አልተሸነፈም።

ኤቨርተን ከሜዳው ውጪ ያለው ውጤት ዝቅተኛ በመሆኑ በሜዳው የሚያደርገው ጨዋታ ላይ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅበታል።

ግምት፡ ኤቨርተን 1 -1 ብሬንትፈርድ

ሊድስ ከ ብራይተን

ሊድስ ከ ብራይተን

ሊድስም እንደ ኤቨርተን ሁሉ በሜዳው ውጤት መሰብሰብ ይኖርበታል።

ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ጎል ብቻ ማስቆጠሩ ያለበትን ችግር ያሳያል።

ብራይተን በሌላ በኩል በነጻነት በመጫወት ዘንደሮ እስከ አራት ባለው ደረጃ ውስጥ ለመጨረስ የሚያስችል አቋም አሳይቷል።

ሊድስ በደጋፊዎች ቢታገዝም ውጤት ለማስመዝገብ በወኔ መጫወት ይኖርበታል።

ግምት፡ ሊድስ 1 - 2 ብራይተን

ብሬንዳን ሮጀርስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሌስተር ከ ቼልሲ፤ ይህን ጨዋታ ለአስልጣኝ ሮጀርስ እጅግ ወሳኝ ነው

ሌስተር ከ ቼልሲ

ሌስተር ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች በመሸነፉ አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ ጫና ውስጥ ገብተዋል።

አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ በዚህ ጨዋታ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ካልቻሉ ደጋፊውም ፊቱን ሊያዞርባቸው ይችላል።

ቼልሲ ረቡዕ ዕለት ዶርትሙንድን በቻምፒየንስ ሊጉ ማሸነፉ ብርታት ስለሚሆነው ለሌስተር ከባድ ይሆንበታል።

ቼልሲ ብዙ ጎል ማስቆጠር ባይችልም የሌስተር የተከላካይ መስመር ግን አስተማማኝ አይደለም።

ግምት፡ ሌስተር 0 - 1 ቼልሲ

ቶተነሃም ከ ፎረስት

ቶተንሃም ከ ኖቲንግሃም ፎረስት

በቶተንሃም ወጥ ባልሆነ አቋም ግራ ተጋብቻለሁ።

የአንቶኒዮ ኮንቴ ቡድን አራተኛ ደረጃን ለመያዝ ብቻ ነው እየተጫወተ የሚገኘው።

ከሻቻምፒዮንስ ሊግ መሰናበታቸውን ተከትሎ ይህንን ጨዋታ በማሸነፍ ምላሽ ለመስጠት ይጫወታሉ።

ፎረስት በበኩሉ ከሜዳው ውጭ ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች አንድ ብቻ አሸንፎ ሦስት አቻ ወጥቷል።

ግምት፡ ቶተንሃም 3 - 1 ኖቲንግሃም ፎረስት

ክሪስታል ፓላስ ከ ማንቸስተር ሲቲ

ክሪስታል ፓላስ ከ ማንችስተር ሲቲ

ሲቲ ባለፈው ሳምንት ከኒውካስል ጋር በነበረው ጨዋታ የበላይነት ባያሳይም ሦስት ነጥብ አሳክቷል።

አሁን እያሸነፉ አርሰናል ላይ ጫና የሚያሳድሩበት ጊዜ ነው።

ከአርቢ ሌፕዚንግ ጋር ያለውን የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ከግምት በማስገባት ፔፕ ጋርዲዮላ ተጫዋቾችን ቀያይረው ይጠቀማሉ።

የፊል ፎደን በጥንካሬ መመለስ ለቡድኑ በጥሩ ሰዓት የመጣ ይመስላል።

ግምት፡ ፓላስ 1 - 2 ሲቲ

እሑድ

ፉልሃም ከ አርሰናል

ፉልሃም ከ አርሰናል

ይህ ድንቅ ጨዋታ እንደሚሆን እጠብቃለሁ። አርሰናልም የሚፈተንበት ይሆናል።

አርሰናል ድንቅ ውጤት እያስመዘገቡ ቢሆንም የአጥቂው መስመር ላይ ያለው መሳሳት ያሳስበኛል።

ዩሮፓ ሊግ ላይ መሳተፋቸው ሐሳባቸውን ሊከፋፍል ቢችልም ትኩረታቸውን ፕሪሚየር ሊጉ ላይ ማድርግ ይጠበቅባቸዋል።

ፉልሃምም በድንቅ አቋም ላይ ይገኛል።

ጨዋታው ከባድ ፉክክር የሚደረግበት ሲሆን፣ አርሰናል እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ።

ግምት፡ ፉልሃም 1 - 2 አርሰናል

ዩናይትድ ከ ሳውዝሃምፕተን

ማንችስተር ዩናይትድ ከ ሳውዝሃምፕተን

ማርከስ ራሽፈርድ በሊቨርፑል በተሸነፉበት ጨዋታ ተጫዋቾቹ ተስፋ ቆርጠው ነበር መባሉን ቢያስተባብልም በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ አልነበሩም።

ቀኑ ለዩናይትድ መጥፎ ከመሆኑም በላይ ለቀጣይ ዓመታትም አብሯቸው የሚኖር የታሪክ ጠበሳ ነው።

ዩናይትድ በዚህ ጨዋታ ምላሽ መስጠት የሚገባው ሲሆን፣ ይህንም ያደርገዋል ብዬም አስባለሁ።

ሳውዝሃምፕተን ከሌስተር ጋር የነበረውን ጨዋታ ቢያሸንፍም የቴን ሃግ ቡድን በእልህ እንደሚጫወት እና ሦስት ነጥቡን እንደሚያሳካ እገምታለሁ።

ግምት፡ ዩናይትድ 3 - 0 ሳውዝሃምፐተን

ቀይ መስመር

ዌስት ሃም ከ አስቶን ቪላ

ዌስት ሃም ባለፈው ሳምንት በብራይተን የደረሰበት ሽንፈት መጥፎ የሚባል ነበር።

ዴቪድ ሞዬስ በዚህ ጨዋታ ውጤት ማስመዝገብ አለባቸው።

አስቶን ቪላ አስቸጋሪ ተጋጣሚ ሲሆን አቻ መለያየት ደግሞ የዌስት ሃምን ደጋፊዎች አያስደስትም።

ቪላ ይህንን ጨዋታ እንደሚያሸንፍ ብገምትም የቀድሞ አጥቂያቸው ዳኒ ኢንግስ ለዌስት ሃም እንደሚያስቆጥር አስባለሁ።

ግምት፡ ዌስት ሃም 1 - 1 አስቶን ቪላ

ኒውካስል ከ ዎልቭስ

ኒውካስል ከ ዎልቭስ

ለ315 ደቂቃዎች ጎል ያላስቆጠረው እና ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ያላሸነፈው ኒውካስል ወደ ድል መመለስ አለበት።

ባለፈው ሳምንት ከማንችስተር ሲቲ ጋር ጥሩ ዕድሎችን መፍጠር ቢችልም ኳስ እና መረብን የሚያገናኝ አጥቂ ይፈልጋል።

ቡድኑ እስከ ፊት መስመሩ ድረስ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን በደጋፊዎች መታጀቡ ውጤታማ ያደርገዋል።

ባለፈው ሳምንት ቶተንሃምን ያሸነፉት ዎልቭሶች በዚህ ጨዋታ ለኒውካስል ፈተና ሆነው ያመሻሉ።

ግምት፡ ኒውካስል 1 - 1 ዎልቭስ