ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአዲሱ የመሬት ሕጓ ምክንያት ትራምፕ ለደቡብ አፍሪካ የሚሰጥ ድጋፍ እንዲቋረጥ አዘዙ
ደቡብ አፍሪካ ባወጣችው አዲስ የመሬት ሕግ ምክንያት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለአገሪቱ የምትሰጠው የገንዘብ ድጋፍ እንዲቋረጥ የሚያደርግ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈረሙ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በደቡብ አፍሪካ ላይ ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው።
ትራምፕ ትዕዛዙን ያስተላለፉት አዲሱ የመሬት ሕግ የሰዎችን መብት የሚጥስ በመሆኑ እና ደቡብ አፍሪካ ከጋዘው ጦርነት ጋር በተያያዘ እስራኤል የዘር ማጥፋት ፈጽማለች በሚል በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ክስ በመመሥረቷ ነው።
በሁለቱ አገራት መካከል ውዝግብ የተፈጠረው ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከተመለሱ ከሳምንት በኋላ ምንም ዓይነት ማስረጃ ሳያቀርቡ "ደቡብ አፍሪካ መሬት እየወረሰች ነው" እና "የተወሰኑ ሰዎችን በአስከፊ ሁኔታ እያጠቃች ነው" በማለት አሜሪካ የምትሰጠውን ድጋፍ እደሚያቋርጡ ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ ነው።
የትራምፕ የቅርብ አማካሪ የሆነው እና ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተወለደው ቢሊየነሩ ኢላን መስክ በኤክስ ገጹ ላይ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ለምን "ግልጽ ዘረኛ የሆነ [የመሬት] ባለቤትነት ሕግ" እንዲኖር ፈለጉ ሲል ጠይቋል።
የትራምፕ ውሳኔን በተመለከተ ራማፎሳ አስተያየት ያልሰጡ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ግን ትራምፕ በሰጡት አስተያየት ላይ የአገራቸውን የመሬት ፖሊሲ ተከላክለዋል።
በዚህም አገራቸው የማንንም መሬት አለመውረሷን እና አዲሱ የመሬት ፖሊሲ ዓላማ ፍትሐዊ የመሬት አቅርቦትን ለማረጋገጥ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።
ከአንድ ወር በፊት ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ያወጡት አዲስ የመሬት ሕግ በተወሰኑ ሁኔታዎች ውስጥ መሬትን ያለካሳ ለመውረስ የሚያስችል ነው።
በደቡብ አፍሪካ ዘረኛው የአፓርታይድ ሥርዓት ከተወገደ ከ30 ዓመታት በኋላ የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል። በአገሪቱ አብዛኛው የግል መሬት የተያዘው በነጮች ነው።
ባለፉት ዓመታት መንግሥት የመሬት ይዞታ ፖሊሲ ለውጥ እንዲያደርግ እና በዘር መድልዎ ዘመን የተፈጸሙ ኢፍትሃዊነቶችን እንዲያስተካከል ጥሪ ሲቀርብለት ቆይቷል።
አዲሱ የደቡብ አፍሪካ የመሬት ሕግ "ፍትሐዊ ሲሆን፣ ለሁሉም እንዲዳረስ እና የሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሲሆን" ያለካሳ መሬት እንዲወረስ ይፈቅዳል።
ይህም የመሬት ይዞታው ጥቅም ላይ ያልዋለ ሲሆን እና የማልማት ዕቅድ ሳይኖር ወይም ገንዘብ የማያስገኝ ከሆነ ወይም ሕዝቡ ላይ ጉዳት የሚያስከትል ከሆነ መሬት ከሚወረስባቸው ምክንያቶች ውስጥ ተካቷል።
ይህንን የደቡብ አፍሪካ መንግሥትን ውሳኔ በመቃወም ትራምፕ ያወጡት ትዕዛዝ ላይ አሜሪካ "በአገሩ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን መብት የሚጥስ መንግሥትን ልትደግፍ አትችልም" በማለት "ይህ ፍትሐዊ ያልሆነ እና ከሞራል ተቃራኒ የሆነ ድርጊት አስከቀጠለ ድረስ" አሜሪካ እርዳታ እና ድጋፍ አትሰጥም ብለዋል።
በተጨማሪም የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው ደቡብ አፍሪካውያን ገበሬዎችን እና ቤተሰቦቻቸው እንደ ስደተኛ በአሜሪካ እንዲሰፍሩ ለማድረግ ዕቅድ እንደሚዘጋጅ ገልጿል።
የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ እስራኤል ጋዛ ውስጥ የዘር ማጥፋት ፈጽማለች በሚል ለዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት በቀረበው ክስ ላይ የነበራት ሚና ተጠቅሷል።
"በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ በአሜሪካ እና በወዳጇቿ ላይ ተቀናቃኝ አቀም ወስዳለች። በዚህም ሐማስን ሳይሆን እስራኤልን በዘር ማጥፋት በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ከሳለች። እንዲሁም ከኢራን ጋር በንግድ፣ በወታደራዊ እና በኒውክሌር ያላትን ግንኙነት አጠናክራለች" ሲሉ ከሰዋል።