ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከ18 ወራት በኋላ በሚካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ 40 አገራት ያህል አድማ ሊመቱ ይችላሉ ተባለ
ከዓመት ከስድስት ወር በኋላ የሚካሄደውን የፓሪስ ኦሊምፒክ እስከ 40 አገራት ያክል አድማ ሊመቱ እንደሚችሉ ፖላንድ አስጠነቀቀች።
የፖላንድ የስፖርት እና ቱሪዝም ሚኒስትር ካሚል ቦርትኒዙክ የፓሪስ ኦሊምፒክ ትርጉም አልባ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ይህ የሚስትሩ አስተያየት የተሰማው ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በፓሪሱ 2024 ኦሊምፒክ የሩሲያ እና ቤላሩስ ዜጋ አትሌቶች እንዲሳተፉ ለመፍቀድ ማቀዱን ፖላንድ፣ ሊቱኒያ፣ ኢስቶኒያ እና ላትቪያ በጋራ መቃወማቸውን ተከትሎ ነው።
ዩክሬን የሁለቱ አገራት አትሌቶች የሚሳተፉ ከሆነ በውድድሩ አልገኝም ብላለች።
የኦሊምፒክ ኮሚቴው ግን በውድድሩ ላይ አድማ ማድረግ ትርፉ “አትሌቶችን መቅጣት ብቻ ነው” ብሏል።
የፖላንድ የስፖርት እና የቱሪዝም ሚንስትሩ የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ከሳምንት በኋላ ከሚያደርገው ስብሰባ በፊት ግሬት ብሪቴን፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ካናዳን ጨምሮ 40 አገራት ውድድሩ ላይ አድማ እንዲመቱ ማሰባሰብ ይቻላል ብለዋል።
ኮሚቴው ባለፈው ሳምንት የሩሲያ እና የቤላሩስ አትሌቶች ገለልተኛ በሆነ ሰንደቅ ዓላማ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ተሳታፊ ሊሆኑ የሚችሉበትን አማራጮች አጤናለሁ ብሎ ነው።
“የትኛውም አትሌት በፓስፖርቱ ምክንያት ከውድድር መታገድ የለበትም” ብሏል።
የዩክሬን የስፖርት ሚኒስትር ቫድያም ጉትሳኢት የሩሲያ እና የቤላሩስ አትሌቶች ታግደው እንዲቆዩ የስፖርት አካላት ከዓለም ፌዴሬሽኖች ጋር ንግገራቸውን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ማድረጓን ተከትሎ የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሩሲያ እና ቤላሩስ አትሌቶችን አግዶ ይገኛል።
የዓለም አቀፉ የኦሊምፖክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ቶማስ ባች ኮሚቴው ይህን ውሳኔ አስተላልፎ የነበረው የሁለቱን አገራት አትሌቶች ፍላጎት ለመጠበቅ ታስቦ እንደነበረ ገልጸው አሁን ላይ አትሌቶቹ ከውድድሮች ሊገለሉ አይገባም ብለዋል።
ትናንት ሐሙስ ጥር 25/2015 ዓ.ም. የላትቪያ፣ ሉቲኒያ፣ ኢስቶኒያ እና ፖላንድ የስፖርት ሚኒስትሮች በጋራ ባወጡት መግለጫ ኮሚቴው የሩሲያ እና የቤላሩስ አትሌቶችን በገለልተኛ ሰንደቅ ዓላማ እንዲወዳደሩ እንኳ የመፍቀዱ እቅድ ውድቅ መደረግ አለበት ብለዋል።
አገራቱ ሌሎች ዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማት እና ፌዴሬሽኖች የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት እስኪያበቃ ድረስ የሩሲያ እና ቤላሩስ አትሌቶችን ከዓለም አቀፍ ውድድሮች አግደው እንዲያቆዩ ጠይቀዋል።
አሜሪካ በበኩሏ የሩሲያ እና የቤላሩስ የስፖርት ተቋማት ከዓለም አቀፍ ወድድሮች እንዲታገዱ እና የስፖርት ውድድሮች በአገራቱ እንዳይሰራጭ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች።
የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ካሪን ጄን-ፒር አትሌቶቹ በኦሊምፒክ ጨዋታው ላይ እንዲሳተፉ የሚፈቀድላቸው ከሆነ ሩሲያ እና ቤላሩስን ሳይወክሉ ገለልተኛ ሆነው መቅረብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም እንዲሁ የሁለቱ አገራት አትሌቶች በፓሪሱ ኦሊምፒክ እንዳይሳተፉ እንደምትደግፍ ገልጻለች።