ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩስያ ጥቃቶች ዒላማቸውን የሃይል ማመንጫዎች ላይ አድርገዋል - ዜለንስኪ
ሩሲያ በዩክሬን የሃይል ማመንጫዎች ላይ ያነጣጠረ “አዲስ መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን” መጀመሯን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ገለጹ።
ጥቃቶቹ በምዕራብ፣ መካከለኛው፣ ደቡብ እና ምስራቅ የዩክሬን ዒላማ በማድረግ “መጠነ ሰፊ” መሆናቸውንም ተናግረዋል ።
1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ቤቶች መብራት እንደሌላቸው ኪዬቭ አስታውቃለች።
ዜለንስኪ አክለውም አብዛኞቹ የሩስያ ሚሳኤሎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃትን ማምከን መቻሉን እና ተመሳሳይ ጥቃቶችም የዩክሬን ወታደራዊ ግስጋሴን እንደማይገታው ተናግረዋል።
"በእርግጥ እስካሁን መቶ በመቶ የሩስያ ሚሳኤሎችን እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ጥቃት የመመከት ቴክኒካል አቅም የለንም:: በአጋሮቻችን እርዳታ ቀስ በቀስ እናሳካዋለን። በዚህ እርግጠኛ ነኝ" ብለዋል የዩክሬን መሪ በቅዳሜ ረፋድ የቪዲዮው መልዕክታቸው።
ካለፈው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ በተፈጸመ የአየር ድብደባ አንድ ሶስተኛ የሚጠጉ የዩክሬን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ወድመዋል።
የቅርብ ጊዜዎቹ ጥቃቶች የተፈጸሙት ከዋና ከተማዋ ኪዬቭ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ የሚገኘው ቼርካሲ እና በምዕራብ በኩል የሚገኘው ክሜልኒትስኪ ከተማ ይገኙበታል።
የአየር ድብደባ እና የሃይል መቆራረጥ በኦዴሳ፣ ሪቭኔ እና ሉስክ ተከስቷል።
ብሔራዊ ኤሌክትሪክ ድርጅት ዩክሬኔርጎ እንዳስታወቀው ጥቃቶቹ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከደረሱት ከፍተኛ የቦምብ ጥቃቶች የበለጠ ጉዳት አድርሰዋል።
ፕሬዝደንት ዘሌንስኪ እንደተናገሩት ቅዳሜ ዕለት 36 ሮኬቶች የተወነጨፉ ሲሆን አብዛኞቹም መክነዋል።
የሊቪቭ ከተማ ምክትል ከንቲባ ሰርሂ ኪራል ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሩሲያ ስትራቴጂ ከክረምቱ በፊት ወሳኝ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ከጥቅም ውጭ በማድረግ እና ጦርነቱን ወደሌሎች አካባቢዎች ማስፋት ነው።
"የዩክሬን ታጣቂ ሃይሎች ወደ ፊት በገሰገሱ ቁጥር ሩሲያ በሲቪሎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እና ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ለማጥቃት የተቻላትን ሁሉ ታደርጋለች" ሲል ተናግረዋል ።
አርብ ዕለት በሞስኮ ሃይሎች ቁጥጥር ስር የሚገኘውንና በኬርሰን ክልል ውስጥ ያለው የውሃ ሃይል ማመንጫ ግድብ ላይ ፈንጂ አጥምዳለች ሲሉ ዜለንስኪ ሩሲያን ከሰዋል።
የካኮቭካ የሃይል ማመንጫ ጣቢያ ከወደመ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የጎርፍ አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ተናግረዋል።
ሩሲያ ግድቡን ለማፍረስ አቅዳለች መባሏን አስተባብላ ዩክሬን ሚሳኤል እየተኮሰችበት እንደሆነ ተናግራለች።
የዩክሬን ጦር ወደ ፊት እየገሰገሰ ባለበት ወቅት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሠላማዊ ሰዎች የኬርሰን ከተማን ለቀው እየወጡ ነው።
ቅዳሜ ዕለት ከሩሲያ ባለስልጣናት አዲስ በድጋሚ በወጣው መመሪያ መሠረት ሰላማዊ ነዋሪዎች “በፍጥነት” እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቅዳሜ የሩስያ ወታደሮች በኬርሶን ግዛት ውስጥ የሚገኙ ቻሪቭን እና ቻካሎቭን የተባሉ መንደሮችን ለቀው መውጣታቸውን የዩክሬን ሃይሎች ተናግረዋል። ይህ ግን በገለልተኛ አካል አልተረጋገጠም።
ከድንበር አቅራቢያ በሚገኘው የሩሲያ የቤልጎሮድ ክልል አስተዳዳሪ እንዳሉት በዩክሬን በተፈጸመ ጥቃት ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።