በደቡብ አፍሪካ ለፋሲካ በዓል መንገደኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አውቶብስ ተገልብጦ 45 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Heidi Giokos
በደቡብ አፍሪካ ለፋሲካ በዓል መንገደኞችን ከጎረቤት አገር ቦትስዋና አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አውቶብስ ተገልብጦ የ45 ሰዎች ሕይወት አለፈ።
የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት ከድልድልይ ላይ ወደ 50 ሜትር ገደል በወደቀው አውቶብስ ውስጥ ከነበሩት ተሳፋሪዎች የ8 ዓመት ሴት ልጅ ብቻ በሕይወት መገኘቷን አስታውቀዋል።
ከሞት የተረፈችው ብቸኛዋ የስምንት ዓመት ልጅ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባትም ተገልጿል።
በሰሜን ምሥራቅ ሊምፖፖ ግዛት አደጋው የደረሰበት አውቶብስ የድልድዩን መከላከያ ጥሶ ቁልቁል ወርዶ ከመሬት ጋር ሲጋጭ በእሳት መያያዙ ተነግሯል።
ተሳፋሪዎቹ ከቦትስዋና ዋና ከተማ ጋቦሮኔ ወደ ሞሪያ ከተማ በአውሮፓውያን አቆጣጠር በመጪው እሁድ ለሚከበረው የፋሲካ በዓል መንፈሳዊ አገልግሎት ሲጓዙ የነበሩ ሃይማኖተኞች ነበሩ።
የአውሮፓውያንን የቀን አቆጣጠር የሚከተሉ ክርስቲያኞች የስቅለት በዓልን ዛሬ ዓርብ መጋቢት 20/2016 ዓ.ም. እያከበሩ ሲሆን የትንሳዔ በዓልን ደግሞ የፊታችን እሁድ መጋቢት 22 ያከብራሉ።
ተሽከርካሪው ከጆሃንስበርግ በስተሰሜን 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ካለው ድልድይ መውደቁን የደቡብ አፍሪካው ኤስኤቢሲ ቀድሞ ዘግቧል።
የሟቾችን አስክሬን የማውጣቱ ሥራ እስከ ሐሙስ ምሽት ድረስ የቀጠለ ሲሆን ሕይወታቸውን ካጡት ሰዎች መካከል የተወሰኑትን አስከሬን ለማግኘት አስቸጋሪ እንደነበረ ተነግሯል።
የአደጋውን ቦታ የጎበኙት የደቡብ አፍሪካ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሲንዲሲዌ ቺኩንጋ በአውቶብሱ አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎች ቤተሰቦች ሐዘናቸውን ገልፀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Limpopo Department of Transport
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አስከሬኖቹን ወደ አገራቸው እንደሚመልስ እና የአደጋውን መንስኤ እንደሚመረመር ተናግረዋል።
“በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ጸሎታችን ከእናንተ ጋር ነው። በዚህ የትንሳኤ በዓል ሰሞን ብዙ ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ ስለሚጓጓዙ ሁልጊዜ በኃላፊነት በማሽከርከር ከፍተኛ ጥንቃቄ እንድታደርጉ” ሲሉም አሳስበዋል።
ደቡብ አፍሪካ ዝቅተኛ የመንገድ ደኅንነት ካላቸው አገራት መካከል አንዷ ናት።
ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ለትንሳኤ በዓል ባስተላለፉት መልዕክት ዜጐች “ደኅንነቱ የተጠበቀ ፋሲካ ለማክበር የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ” አደራ ብለዋል።












