የዓለማችን ውቅያኖሶች 171 ትሪሊዮን የፕላስቲክ ምርት ታቅፈዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሳይንቲስቶች የዓለማችን ውቅያኖሶች ቢያንስ 171 ትሪሊዮን የፕላስቲክ ምርቶች ታቅፈው ይኖራሉ እያሉ ነው።
የፕላስቲክ ምርት ዓሳና ሌሎች ውቅያኖስን ቤታቸው ያደረጉ እንስሳትን የሚገድል ሲሆን ፕላስቲክን ከውቅያኖስ ለማስወገድ መቶ ዓመት ሊወስድ ይችላል።
አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው በፈረንጆቹ 2005 ውቅያኖስች ላይ ሲንሳፈፍ የነበረው ፕላስቲክ ቁጥር 16 ትሪሊዮን ነበር።
እርምጃ ካልተወሰደ በ2040 አሁን ካለው ቁጥር ሶስት እጥፍ ሊሆን ይችላል ሲሉ ሳይንቲስቶች ያስጠነቅቃሉ።
ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት ሃገራት ቢያንስ 30 በመቶ ውቅያኖስን ለመጠበቅ ስምምነት ገብተዋል።
የፕላስቲክ ምርቶቹ በቅርቡ ወደ ውቅያኖስ ተጥለው እየተንሳፈፉ ያሉ በጊዜ ብቻ የተሰባበሩ ናቸው ይላሉ የጥናት ቡድኑ ኃላፊ ዶክተር ማርከስ ኤሪክሰን።
እንደ ውሃ ኮዳ ያሉ አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ፕላስቲኮች በፀሐይ ብርሃንና ‘ሜካኒካል ዲግሪዴሽን’ በተባለ ሂደት አማካይነት በጊዜ ሂደት ይበታተናሉ።
እንደ አሳ ነባሪ፣ ሲበርድ፣ የባህር ዔሊና ዓሳ ያሉ እንስሳት የተበታተነውን ፕላስቲክ ከተመገቡ በኋላ ሆዳቸው ስለሚሞላ በረሃብ ምክንያት ይሞታሉ።
ይህ ብቻ አይደለም የፕላስቲክ ምርት የምንጠጣው ውሃ ውስጥ ተገኝቶ ያውቃል።
በጣም ጥቃቅን የሚባሉ የፕላስቲክ ምርቶች ሳንባ፣ ደም ሥርና ፕላሴንታችን ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ።
ነገር ግን ሳይንቲስቶች ጥቃቅን የፕላስቲክ ምርቶች የሰው ልጅ ላይ ጉዳት ያደርሳሉ ወይ የሚለው እስካሁን ምላሽ እንዳላገኘ ይናገራሉ።
ውቅያኖሶች ያዘሉት የፕላስቲክ ምርት በ15 ዓመታት ውስጥ ከ16 ትሪሊዮን ወደ 171 ትሪሊዮን አድጓል።
ከ2005 ዓመት በፊት በነበረው ጊዜ ውቅያኖስ ላይ የሚራገፈው የፕላስቲክ ምርት እጅግ አናሳ ነበር ይላሉ ኤሪክሰን።
አጥኚዎቹ እንደሚያምኑት ከ2005 በፊት በነበረው ጊዜ በርካታ ሃገራት የፕላስቲክ ምርት ወደ ውቅያኖስ መጣልን ይከለክሉ ነበር።
በጣም በርካታ የፕላስቲክ ምርት ያለበት ውቅያኖስ ሰሜን አትላንቲክ ሲሆን ግሬት ፓሲፊክ ጋርቤጅ ፓች የተባለው ሥፍራም በርካታ ፕላስቲክ ተገኝቶበታል።
ግሬት ፓሲፊክ ጋርቤጅ ፓች ከዓይን ዕይታ በላይ የሆነ በርካታ ቆሻሻ ተከምሮበት የሚታይ ሥፍራ ነው።
ሳይንቲስቶቹ ውቅያኖሶችን ከማፅዳትና የፕላስቲክ ምርቶችን መልሶ ከመጠቀም ይልቅ የሚመረተውን ፕላስቲክ መቀነሱ የተሻለ መፍትሔ ነው ብለው ያምናሉ።












