ካማላ ሃሪስ የሚኒሶታው ገዢ ቲም ዎልዝ የምርጫ አጋራቸው አድርገው መረጡ

ሃሪስ እና ዎልዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሃሪስ እና ዎልዝ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሚቀጥለው ዓመት ኅዳር ለሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ የሚኒሶታውን አገረ ገዢ ቲም ዎልዝ ምክትላቸው በመሆን የምርጫ አጋራቸው እንዲሆኑ መረጡ።

ከቀናት በፊት በይፋ የዴሞክራቶች ዕጩ ተደርገው የቀረቡት ካማላ ሃሪስ ቀጣዩን ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ ቲም ዎልዝ ምክትል ፕሬዝዳንት ይሆናሉ።

በኅዳር 2016 ዓ.ም. ምርጫ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ እና የቀድሞው መምህር ቲም ዎልዝ ከሪፓብሊካኖቹ ዶናልድ ትራምፕ እና ጄዲ ቫንስ ከባድ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።

ካማላ የሚኒሶታ ግዛት አስተዳዳሪን ምክትላቸው እንሆኑ የምርጫ አጋራቸው አድርገው መምረጣቸውን ቀደም ሲል ባወጡት ረዘም ያለ መግለጫ አስታውቀዋል።

ሃሪስ እና ዎልዝ በፊላዴልፊያ በምርጫ ቅስቀሳ ላይ አብረው ተገኝተዋል።

እኒህ አንደበተርቱዕ፣ የስፖርት አፍቃሪ እና የቀድሞ የጦር ሠራዊት አባል የነበሩት አንጋፋው ፖለቲከኛ፤ ዴሞክራቶች ወግ አጥባቂ የሆኑ ድምጽ ሰጪዎችን ድጋፍ እንዲያገኙ ይረዳሉ የሚል ግምት አለ።

በገጠራማ ኔብራስካ ግዛት የተወለዱት የ60 ዓመቱ ዎልዝ የአሜሪካ ብሔራዊ ዘብ ጦርን በ17 ዓመታቸው ተቀላቅለው ለ24 ዓመታት አገልግለዋል።

ከወታደር ቤት መልስ በሕዝብ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ሆነው የቆዩት ዎልዝ፣ በትምህርት ቤት ቆይታቸው ከመምህርነታቸው በተጨማሪ የአሜሪካ እግር ኳስ አሠልጣኝ ነበሩ።

ፊታቸውን ወደ ፖለቲካ ከዞሩ በኋላ በአሜሪካ ኮንግረስ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በመቆየት በአውሮፓውያኑ 2018 የሚኒሶታ ግዛት ገዢ ሆነው ተመርጠዋል።

በመጀመሪያው የግዛት አስተዳዳሪ የሥልጣን ዘመናቸው ወቅት የኮቪድ-19 ሥርጭት እንዲሁም ጆርጅ ፍሎይድ የተባለው ጥቁር አሜሪካዊ በነጭ ፖሊስ መገደል ፈታኝ ሆኖባቸው ነበር።

ይሁን እንጂ ዎልዝ እአአ 2022 ላይ ዳግም የሚኒሶታ ገዢ ሆነው ከተመረጡ በኋላ ባለፉት ዓመታት በግዛቷ አነስተኛ ገቢ ላላቸው የግብር ቅነሳ አድርገዋል እንዲሁም ሠራተኞች እየተከፈላቸው እረፍት እንዲያገኙ አስችለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ቲም ዎልዝ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ማስጀመራቸው ስማቸውን በመልካም የሚያስነሳ ነው።