አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ ከሻምፒዮንስ ሊግ ውጭ ሆኑ

ታትሟል

በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የእንግሊዞቹ አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ ሲሰናበቱ ባየር ሙኒክ እና ሪያል ማድሪድ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል።

በአሊያንዝ አሬና በተደረገ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ባየር ሙኒክ አርሰናልን 1 ለ 0 በማሸነፍ ነው ግማሽ ፍጻሜውን የተቀላቀለው።

ጆሹዋ ኪሚች በ63ኛው ደቂቃ በግንባር ያስቆጠራት ጎል ቡድኑን ወደ ቀጣዩ ዙር ለማሳለፍ ችላለች።

በመጀመሪያው ዙር የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ኤምሬትስ ላይ 2 አቻ ተለያይተው ነበር።

በዚህም ባየር ሙኒክ 3 ለ 2 በሆነ በአጠቃላይ ውጤት ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

ቋሚ ተሰላፊዎቹን በጉዳት እና በቅጣት ማሰለፍ ያልቻለው ሙኒክ ዘንድሮ በቡንደስ ሊጋው ደካማ ውድድር ዘመን ቢያሳልፍም በአውሮፓ መድረክ ጥሩ በመጓዝ ላይ ይገኛል።

በሌላ የምሽቱ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ሪያል ማድሪድ በመለያ ምት ማንቸስተር ሲቲን በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

ሁለቱ ቡድኖች ስፔን ላይ ባደረጉት መጀመሪያው ዙር ጨዋታ 3 አቻ ተለያይተው ነበር።

ትላንት ምሽት ሪያል ማድሪድ ኤምሬትስ ስታዲየም ላይ በብራዚላዊው ሮድሪጎ ጎል ቀዳሚ ለመሆን ችሏል።

የማንቸስተር ሲቲው ኬቪን ደብራይን በ76ኛው ደቂቃ ቡድኑን አቻ አድርጓል።

በጨዋታው 33 ሙከራ አድርገው 18 የማዕዘን ምቶችን ያገኙት ሲቲዎች የፈጠሯቸውን አጋጣሚዎች ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

ጨዋታው በድምር ውጤት 4 ለ 4 በመጠናቀቁም ሁለቱ ቡድኖች ወደ መለያ ምት አቅንተዋል።

በመለያ ምቱ ማድሪድ 4 ለ 3 ለማሸነፍ ችሏል።

በሪያል ማድሪድ በኩል አማካዩ ሞድሪች መለያ ምቱን ሲስት በሲቲ በኩል ደግሞ በርናንዶ ሲልቫ እና ኮቫቺች የመለያ ምት ስተዋል።

በሁለቱ ጨዋታዎች ሁለቱ እንግሊዝ ቡድኖች ከሻምፒዮንስ ሊግ ውጭ መሆናቸው አምስተኛ የፕሪሚየር ሊጉ ቡድን በመድረኩ ላይ የመወዳደር ዕድሉን እንዲጠብ ሆኗል።

በመደበኛነት አራት የእንግሊዝ ቡድኖች በሻምፐፒዮንስ ሊግ የሚሳተፉ ሲሆን የየአገራቱ ቡድኖች በሚያስመዘግቡት ውጤት ተጨማሪ ቢድኖች እንዲሳተፉ ዕድል የሚሰጥበት አሠራር አለ።

በውጤት መሠረት በሚሰጠው ተጨማሪ ዕድል ጣሊያን ቀዳሚ ስትሆን ቀጣዩን ቦታ ለመያዝ እንግሊዝ እና ጀርመን ቡድኖች ተፋጠዋል።

ከሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች በፊት ጀርመን በአነስተኛ ነጥብ እንግሊዝ የምትመራ ቢሆንም የቦርስያ ዶርትሙንድ እና የባየር ሙኒክ ግማሽ ፍጻሜ መቀላቀል እንዲሁም የማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ከውድድሩ ውጭ መሆን ልዩነቱን አስፍቶታል።

አሁንም ቢሆን እንግሊዝ ውጤቱን ለመቀየር በዩሮፓ ሊግ እና በኮንፈረንስ ሊግ በሚሳተፉ ቡድኖቿ ውጤቱን መቀልበስ ትችላለች።

በዩሮፓ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች በአትላንታ 3 ለ 0 ተሸነፈው ሊቨርፑል እና በባየር ሊቨርኩሰን 2 ለ 0 የተሸነፈው ዌስ ትሃም ውጤታቸውን ለመቅለበስ ትልቅ ፈተና ይገጥማቸዋል።

በአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ የሚሳተፈው አስቶን ቪላ በመጀመሪያው ዙር ግጥሚያ ሊልን 2 ለ 1 አሸንፏል።

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የግማስ ፍጻሜ ጨዋታዎች ከሁለት ሳምንት በኋላ ሲከናወን ቦርስያ ዶርትሙንድ ከፒኤስጂ እና ባየር ሙኒክ ከሪያል ማድሪድ እንዲጫወቱ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።