የአየርላንድ መንግሥት ጣቢያ በ5 ሺህ ዩሮ ነጠላ ጫማ በመግዛት ገንዘብ አባክኗል ተብሎ ተወቀሰ

ራያን ተብሪዲ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

ታትሟል

የአየርላንዱ አርቲኢ በ5 ሺህ ዩሮ ነጠላ ጫማ በመግዛት የመንግሥት ገንዘብ አባክኗል ተብሎ ተወቀሰ።

የአየርላንድ ሕዝብ አንደራሴዎች ናቸው ይህን ወቀሳ ያቀረቡት።

ሚድያውን እንዲቆጣጠር የተቋቋመው ኮሚቴ የቀድሞና የወቅቱ የአርቲኢ አለቃዎችና ሠራተኞች ገንዘብ አባክነዋል ሲሉ ወቅሰዋል።

ሚድያው አሉኝ ከሚላቸው አቅራቢዎች አንዱ የሆነው ራያን ተብሪዲ የተሰኘው ግለሰብ ወፈር ያለ ገንዘብ እንደከተፈለው ተገልጧል።

የተከፈለው ገንዘብ ይፋ ባይሆንም ራያን ለኮሚቴው ቀና ትብብሩን እንደማይነሳ ቃል ገብቷል።

አቅራቢው ከ2017 እስከ 2022 ባለው ጊዜ 245 ሺህ ዩሮ በደመወዝ መልክ እንደተከፈለው ጣቢያው ገልጧል።

በዚህ ክፍያ ሳቢያ የቀድሞው የጣቢያው ዳይሬክተር ጀኔራል ሥራቸውን ለመልቀቅ ተገደዋል።

የምሽት ‘ቶክ ሾው’ አቅራቢው የተወሰነውን ክፍያ የተቀበለው በዓይነት እና በአገልግሎት መልክ ነው።

ይህ ማለት ለምሳሌ ጣቢያው ጥሬ ገንዘብ ከሚሰጠው ይልቅ መኪና እና የማስታወቂያ ገቢ ይሰጠው ነበር ማለት ነው።

የጣቢያውን የፋይናንስ አስተዳዳሪ የወቀሱት የፓርላማ አባላት አርቲኢ በመንግሥት ገንዘብ ሲጫወት ነበር ብለዋል።

ከእነዚህ መካከል የሙዚቃ ድግስ [ኮንሰርት] ቲኬት ለመግዛት 18 ሺሕ ዩሮ ገደማ ገንዘብ ያወጣው ተጠቅሷል።

አልፎም 5 ሺህ ዩሮ አውጥቶ 200 ነጠላ ጫማዎች እንደገዛ የኮሚቲው አባል ብሬንዳን ግሪፊን አሳውቀዋል።

የቀድሞው የጣቢያው የቦርድ ሊቀ መንበር ሞያ ሆኸርቲ ቦርዱ ስለአንዳንድ ወጪዎች የሚያውቀው ነገር አልነበረም ብለዋል።

አልፎም ጣቢያው 'ቶይ ሾው ዘ ሙዚካል' የተሰኘ ፕሮግራም አዘጋጅቶ 2.2 ሚሊዮን ዩሮ እንደከሰረ አንድ የኮሚቴው አባል አጋልጠዋል።

አርቲኢ በአየርላንድ መንግሥት የሚተዳደር የራድዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ ነው።

በፈረንጆቹ 1960 የተቋቋመው ጣቢያው በራድዮ፣ ቴሌቪዥን እና በይነ መረብ መንገዶች ፕሮግራሞቹን ያሠራጫል።

ጣቢያው ከፍተኛ ደመወዝ ከሚከፍላቸው 100 ግለሰቦች መካከል 70 በመቶው አመራሮች መሆናቸውም ጨምሮ ተመልክቷል።

ከአመራሮች ወረድ ብለው የሚገኙት በቴሌቪዥንና በራድዮ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ለአድማጭ ተመልካች የሚያደርሱ አቅራቢዎች ናቸው።

የፓርላማው ልዩ ኮሚቴ የሰበሰባቸውን ማስረጃዎችን ተጠቅሞ የድርጅቱን የቀድሞና የአሁን አለቃዎች በመመርመር ላይ ይገኛል።