የፓርላማ አባሉ ጃፓናዊ ዩቲዩበር በሥራ ገበታው ላይ ተገኝቶ ስለማያውቅ ከአባልነት ታገደ

ዮሺካዙ ሂጋሺታኒ

የፎቶው ባለመብት, GAASYY/YOUTUBE

ታትሟል

የጃፓን ምክር ቤት አባል ሆኖ የተመረጠው ታዋቂ ጃፓናዊ ዩቲዩበር በሥራ ገበታው ተገኝቶ ባለማወቁ ከሥራው ታገደ።

ሃሜተኛ በሆኑት የዩቲዩብ ቪዲዮቹ የሚታወቀው ዮሺካዙ ሂጋሺታኒ የሕዝብ ተወካይ ሆኖ ተመርጦ ፓርላማ ሳይገባ የተባረረ የመጀመሪያው ፖለቲከኛ ሆኗል።

ግለሰቡ ከሰባት ወራት በፊት የምክር ቤት አባል ሆኖ የተመረጠ ቢሆንም በአንድ የፓርላማ ስብሰባ ላይ እንኳን ሳይገኝ ቀርቷል ተብሏል።

በዚህም የጃፓን ፓርላማ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ዮሺካዙ ሂጋሺታኒ በሥራ ገበታው ተገኝቶ ሰለማያውቅ የምክር ቤት አባልነቱን አንስቶበታል።

የዲሲፕሊን ኮሚቴው በምክር ቤት አባል ላይ ሊያስተላልፈው የሚችለው ትልቁ ቅጥታ እግድ ሲሆን፣ ይህም ከእአአ 1950 ወዲህ ሁለት የምክር ቤት አባላት ላይ ብቻ ነው ተፈጻሚ የሆነው።

በታዋቂ ሰዎች ዙሪያ የሃሜት ቪዲዮችን በመስራት የሚታወቀውን ግለሰብ መራጮች የአገሪቱ የላይኛው ምክር ቤት አባል አድርገው የመረጡት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ነበር።

ይሁን እንጂ ኑሮውን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሳያደርግ አይቀርም የተባለው ግለሰብ አንድም ቀን በሥራ ገበታው ላይ አልተገኝም፤ በዚህም ‘ሥራ የማይገባው የምክር ቤት አባል’ የሚል ስም አግኝቷል።

የጃፓን መገናኛ ብዙኃን ዮሺካዙ ሂጋሺታኒ በፓርላማ የማይገኘው በማጭበርበር እና የተዋቂ ግለሰቦችን ስም ማጥፋት በሚሉ ወንጀሎች በቁጥጥር ስር እውላለው የሚል ስጋት ስላለነበት ነው ሲሉ ዘግበዋል።

ባለፈው ሳምንት የአገሪቱ ፓርላማ ሂጋሺታኒ በአካል ቀርቦ በሥራ ገበታው ላይ ባለመገኘቱ ይቅርታ እንዲጠይቅ ትዕዛዝ ሰጥቶት ነበር።

የፓርላማ አባሉ ግን ወደ ቶኪዮ ከማቅናት ይልቅ ወደ ቱርክ ተጉዞ በርዕደ መሬት ለተጎዱ ድጋፍ እንዲውል ደሞዙን እንደሚሰጥ በዩቲዩብ ገጹ ላይ ወጥቶ ተናግሯል።

የዮሺካዙ ሂጋሺታኒ ፓርቲ አባል እና የሕዝብ ተወካዩ ሃማዳ ሳቶሺ ምክር ቤቱ የፓርቲ አጋራቸውን የማባረር ሕጋዊ መብት የለውም በማለት ተከራክረዋል።

ነገር ግን ሂጋሺታኒ የውክልና ኃላፊነቱን ለመወጣት ባለመገኘቱ የተበሳጩ የምክር እንደራሴዎች አባሉ እንዲታገድ በዚህ ሳምንት ድምጽ ሰጥተዋል።